የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ይጀመራል

10 Mons Ago
የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ይጀመራል
በኮሎምቢያ ካሊ የሚካሄደው 19ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ይጀመራል። ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በ10 ሴት እና በ9 ወንድ በድምሩ በ19 አትሌቶች ትወከላለች። 800 ሜትር፣ 1 ሺህ 500 ሜትር፣ 3 ሺህ ሜትር፣ 3 ሺህ ሜትር መሰናክል እና 5 ሺህ ሜትር አትሌቶቹ የሚሳትፉባቸው የውድድር አይነቶች ናቸው። በሻምፒዮናው ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን ለውድድሩ አንድ ወር የሚጠጋ ጊዜ ዝግጅት ማድረጉን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። ዛሬ ምሽት በሻምፒዮናው መክፈቻ ቀን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ውድድሮች እንደሚካሄዱ ኢዜአ ዘግቧል። በኮሎምቢያ ካሊ የሚካሄደው 19ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ145 አገራት የተወጣጡ 1 ሺህ 533 አትሌቶች እንደሚሳተፉ የዓለም አትሌቲክስ አስታውቋል። በሻምፒዮናው በ45 የተለያዩ ርቀቶች ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን ሻምፒዮናው እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ይቆያል። ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2021 በኬንያ ካሳራኒ በተካሄደው 18ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና 3 የወርቅ፣ ሰባት የብር እና 2 የነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎችን በማግኘት አራተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።
ግብረመልስ
Top