በ‘ማቴሪያል ሳይንስ’ እና ኬሚካል ምህንድስና ምርምር የነገሱት ፕሮፌሰር ሶስና ኃይሌ!

1 Yr Ago
በ‘ማቴሪያል ሳይንስ’ እና ኬሚካል ምህንድስና ምርምር የነገሱት ፕሮፌሰር ሶስና ኃይሌ!
 
በማቴሪያል እና በኬሚካል ምህንድስና ሳይንስ በዓለም አቀፍ መድረክ አንቱታን ያተረፉት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሶስና ኃይሌ ግለ ታሪካቸው የደመቀ ነው፡፡
 
ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ካስጠሩ መካከል በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት አሜሪካዊ የሆኑት ፕሮፌሰር ሶስና ኃይሌ የተወለዱት በ1958 ዓ.ም በአዲስ አበባ ነው። ፕሮፌሰር ሶስና የህጻንነት ዘመናቸውን ለተወሰኑ ዓመታት በአዲስ አበባ ያሳለፉ ሲሆን በትምህርታቸው ጠንካራ ከሚባሉት ተማሪዎች መካከል የሚመደቡ ነበሩ፡፡የፕሮፌሰር ሶስና የህይወት ጉዞ የተቀየረው በ1970 ዎቹ አጋማሽ በደርግ ዘመነ መንግስት የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ ቤተሰቡ ወደ አሜሪካ በስደት መጓዙ ነበር።
ፕሮፌሰር ሶስና ትምህርታቸውን በሚኒሶታ ጆንስ የመሰናዶ ትምህርት ቤት ገብተው በ1975 ዓ.ም አጠናቀዋል።
በ1978 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪቸውን በማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት በማቴሪያል ሳይንስና በኬሚካል ምህንድስና ማግኘት የቻሉ ሲሆን፤ ሁለተኛ ዲግሪቸውን ደግሞ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ ማሳካት ችለዋል። ፕሮፌሰር ሶስና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ወዳገኙበት የማሳቹሴትስ የቴክኒሎጂ ኢኒስቲትዩት በማቅናት በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ዶክትሬት (PhD) ትምህርታቸውን ለመማር እንዲያስችላቸው በሚወዱት የማቴሪያል ሳይንስና የኬሚካል ምህንድስና ዘርፍ መመረቅ ችለዋል። ዶ/ር ሶስና ከዚህ የተሳካ የትምህርት ጉዟቸው በኋላ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ካገኙበት የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ከማምራታቸው በፊት ሲያትል በሚገኘው በዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት አገልግለዋል፡፡ በዚህ የሶስት ዓመት ቆይታቸውም ሀገራቸውን የሚያኮራና አፍሪካንም የሚያስጠራ ትልልቅ የምርምር ስራዎችን ለመስራት በቅተዋል።
✍️ፕሮፌሰር ሶስና ከ150 በላይ የሆኑ የጥናትና ምርምር ፅሁፎችን በግል እና ከሌሎች ምሁራን ጋር በጋራ በመቀናጀት ሰርተው ለህትመት አብቅተዋል፡፡
✍️አስራ አምስትን በስማቸው የተመዘገቡ ፓተንቶችም አሏቸው።
✍️ከነዚህ የህትመት እና ምርምር ውጤቶች ውስጥ ብዙሃኑ በጠጣር የአዮን ቁስ እና መሳሪያዎች ላይ ያጠነጠኑ ናቸው። በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚያጠነጥኑት የፕሮፌሰር ሶስና ስራዎች መካከል ደግሞ ከዓመታት በፊት የሰሯቸው አዲስ ዓይነት የፊውል ሴል ከሌሎች ፈጠራዎቻቸው መካከል ይጠቀሳል።
✍️በወቅቱ ሶስና ኬሚካሎችን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል በመቀየር ለመኪኖች፣ ኃይል ማመንጫዎች እንዲሁም ሌሎች ኃይልን ለሚጠይቁ ተግባራት ንፁህ የኃይል ምንጭ በመሆን እንዲያገለግል በማሰብ የፊውል ሴሎችን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሻሽል ቁስን ለመስራት አልማ ተነሳች።
✍️ፕሮፌሰር ሶስና በአሁኑ ሰዓት ጠጣር ፊውል ሴሎችን በተለይም ለከባቢ ተስማሚ የኃይል ምንጭ መሆን በሚችሉት ላይ አተኩሮ የሚሰራን የምርምር ቡድን በኃላፊነት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡
✍️በዚህ ረገድ ይህ ቡድን የተለያዩ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ ሲገኝ ከቅርብ ስኬቶቹ መካከልም ውሃና ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን በቴርሞ ኬሚካል ሂደት አማካኝነት በመጠቀም የፀሐይን ኃይል ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ሌላ ምዕራፍን የከፈተ ነበር።
✍️በፕሮፌሰር ሶስና እና ቡድናቸው እየተሰራባቸው ካሉት ስራዎች ውስጥ ፕሩቶንን አስተላላፊ ጠጣር አሲድ እና ፐሮቭስካይት ኤሌክትሮይቶች፣ የኤሌክትሮን እና ኦክስጅን ድብልቅን አስተላላፊ ፍሎሪት እና ፐሮቭስካይት እንዲሁም ኢ-ስቶይኪዮሜትሪክ ኦክሳይዶችን ማበልፀግ ይገኝበታል።
✍️እኝህ ኢትዮጵያዊት እንቁ ተመራማሪ በትልቁ ስማቸውን ከሚያስጠሩ ስራዎቻቸው አንዱ ከሆነው የፊውል ሴል ፈጠራ በተጨማሪ በሴራሚክ ሳይንስ፣ በኤሌክትሮኬሚካል እና በፋንክሽናል ሶሊድ ያደረጓቸው ምርምሮች እና ያሳተሟቸው ፅሁፎች በተሰማሩበጽ የሳይንስ ዘርፍ ከሚኖረው አበርክቶት ባለፈ ለብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያን እና ሴት ተመራማሪዎች የሚኖረው ጠንካራ መልእክት ቀላል የሚባል አይደለም።
✍️ከዚህ ጋር ተያይዞ ፕሮፌሰር ሶስና ኃይሌ ለሰሯቸው ስራ እና ላበረከቱት የምርምር ውጤት እውቅና የሚሆን ሽልማቶችን ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች አግኝተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም ፡-
🏆ኤን ኤስ ኤፍ ከ1986 እስከ 1991 ዓ.ም ያዘጋጀውን ብሔራዊ የታዳጊዎች የምርምር ሽልማትን አሸናፊ ነበሩ።
🏆የሃምበልድ ሕብረት ሽልማት
🏆የፉል ብራይት ሕብረት ሽልማት
🏆የኤቲ እና የቲ ህብረት ምርምር ሽልማትን ማሸነፍ ችለዋል።
🏆ፕሮፌሰር ሶስና የ1993 ዓ.ም ጀቢ ዋግነር ሽልማት
🏆የዓለም አቀፍ የሴራሚክ ማኅበር ሽልማት
🏆ሁለት ሺ ኮብል የተሰኘ ሽልማት እና ሃርዲ አዋርድ የተሰኙ ሽልማቶች ማግኘታቸው ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ የስኬት መገለጫዎቻቸው የአርዓያነት ስብዕናቸውን በዓለም አቀፍ መድረክ ጭምር እንዲጎላ አድርጎታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top