«አንድነታችን ካለፉት ፈተናዎች ታድጎናል፣ ወደ ነገ ተስፋችንም ያደርሰናል!» ውድ ኢትዮጵያውያን

1 Yr Ago
«አንድነታችን  ካለፉት ፈተናዎች ታድጎናል፣ ወደ ነገ ተስፋችንም ያደርሰናል!» ውድ ኢትዮጵያውያን
ውድ ኢትዮጵያውያን
ፈተና ለሀገራችን አዲስ አይደለም። በተለያዩ ጊዜያት ዜጎችን ያስጨነቁ፣ በስጋት ያሸበሩና ተስፋን የተገዳደሩ ጥቂት የማይባሉ የፈተና ምዕራፎችን እንደሕዝብ ተጋፍጠናል። ከሩቅ እስከቅርብ ጠላቶቻችን የመውደቂያና የመፍረሻ ቀናችንን ሲጠብቁ፣ በተደጋጋሚ ከገባንበት ፈተና መንጭቆ ያወጣን የህዝባችን ወንድማማችነት፣ መተማመንና መተባበር ነው። ኢትዮጵያውያን በዓለም መታወቂያችን ይህ በችግርና በፈተና ወቅት ቅራኔዎቻችንን ቸል ብለን በአንድነት መቆማችን ነው።
ከሰሞኑ በሀገራችን የተከሰቱት ሁኔታዎችም ከነዚያ ጊዜያት በተለየ የከበዱ አይደሉም። ነገር ግን ይለያሉ። የሰሞኑ ፈተናዎቻችን ለዘመናት የታደገንን እና እንደህዝብ ያስቀጠለንን ህዝባዊ ውል ለመተርተርና የአንድነታችንን ስረ መሰረት ለማናጋት ያለሙ እንደሆኑ እያየን ነው። የጋራ ዓላማና ራዕይ የሌለን እንዲመስለንና እርስ በርስ በጥርጣሬ እንድንተያይ፣ ከትልቋ መርከባችንን ላይ ዐይናችንን አንስተን ወደ ታንኳዎቻችን እንድናተኩር አቅደው በትንንሽ ቅራኔዎቻችን ውስጥ ትልልቅ ግጭቶችን የሚደግሱልን ታሪካዊ ጠላቶች እንዳሉን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም።
በአንድነት የለበስነው ጋቢ የተሸመነው ከእያንዳንዳችን በተዋጡ ክሮች ነውና፣ የአንዷን ክር መተርተር በቸልታ ማየት የለብንም። የአንድ ክር መተርተር መጨረሻው የት እንደሆነ አይታወቅምና የጋራ ሀገራችንን እንዳያሳጣን እንንቃ።በትንሽ በትልቁ እልህና ጠበኝነትን የሚቆሰቁሱ ሀይሎችን ከምንጊዜውም በላይ በትዕግሥትና ሰከን ብሎ ነገሮችን በጥሞና በመመርመር ማክሸፍ ይገባናል። ጠላቶቻችን በእርስበ እርስ እልህ፣ ትግልና መናቆር እንድናባክነው ያሰቡትን ዕውቀትና ጉልበታችንን፣ በጦርነት፣ በአንበጣ መንጋ፣ በኮሮና ወረርሽኝና በድርቅ የተፈተነች ሀገራችንን ዳግም ለመገንባት እናውለው። በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ሆድ የባሳቸውና የተከፉ ወገኖች በእልህ ወደጥፋትና እልቂት እንዳያመሩን በታላቅ ትዕግስትና መተዛዘን እንተጋገዝ።
«አንድነታችን ካለፉት ፈተናዎች ታድጎናል፣ ወደ ነገ ተስፋችንም ያደርሰናል!»

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top