ደቡብ አፍሪካዊው ዲጄ “ብላክ ኮፊ” የግራሚ ሽልማት አሸናፊ ሆነ

04/04/2022 02:49
ደቡብ አፍሪካዊው ዲጄ “ብላክ ኮፊ” የግራሚ ሽልማት አሸናፊ ሆነ
ደቡብ አፍሪካዊው ዲጄና የሙዚቃ ፕሮዲዩሰር ብላክ ኮፊ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የግራሚ ሽልማት አሸናፊ ሆኗል።
ለ64ኛ ጊዜ በተካሄደው የግራሚ አዋርድ ብላክ ኮፊ በምርጥ ዳንስ ወይም የኤሌክትሮኒክስ አልበም በሚል ዘርፍ ነው አሸናፊ መሆን የቻለው።
ግራሚ አዋርድ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዚህ ዘርፍ ሽልማቱን ያገኘ አፍሪካዊ አርቲስት ባለመኖሩም ብላክ ኮፊ የመጀመሪያው አፍሪካዊ አርቲስት ይሆናል።
የሙዚቃ ባለሙያው ሽልማቱን በተቀበለበት ወቅት እደተናገረው፤ በተሰጠኝ የሙዚቃ ስጦታ የሰዎችን ችግር በመካፈሌ፣ በህይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥማቸውን ማንኛውንም ነገር እንዲያልፉ በመርዳቴ እና በሙዚቃ ስሜት ነፍስን መፈወስ በመቻሌ ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ ብሏል።
በኦሚክሮን ቫይረስ ምክንያት ለወራት ዘግይቶ ትላንት በአሜሪካ ላስ ቬጋስ የተደረገው የ2022 ግራሚ አዋርድ በተለያዩ የሙዚቃ ዘርፎች የታጩ ስራዎችን ለሽልማት አብቅቷል።
በዚህም የዓመቱ ምርጥ አልበም አሜሪካዊው ጆን ባቲስቲ "ዊ አር" በሚለው አልበም ሲያሸንፍ የአመቱ ነጠላ ዜማ እና የአመቱ ምርጥ ቀረፃ በሚለው ደግሞ "ሊቭ ዘ ዶር ኦፕን" የሚለው ነጠላ ዜማ አሸናፊ ሆኗል።
በምርጥ የሬጌ አልበም "ቢዩቲ ኢን ዘ ሳይለንስ" በሚለው አልበሙ የሚታወቀው ሶጃ ባንድ የዓመቱ የግራሚ አዋርድ አሸናፊ መሆን ችሏል።
በህፃናት የሙዚቃ አልበም "ኤ ከለርፉል ዎርልድ" በሚለው አልበሟ የምትታወቀው ህንዳዊቷ የሙዚቃ ባለሙያ ፋሉ አሸናፊ ስትሆን፤ በምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮ ዘርፍ "ፊሪደም" የተሰኘው የጆን ባቲስቲ ሙዚቃ አሸናፊ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
በሌላ በኩል አፍሪካዊቷ የቤኒን ተወላጅ አንጌልኪ ኪዲጆ በዓለም አቀፍ ምርጥ የሙዚቃ አልበም ዘርፍ አሸናፊ በመሆን ትልቅ ስኬት አስመዝግባለች።
ግብረመልስ
Top