ፋኦ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል 138 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አደርጋለሁ አለ

2 Yrs Ago
ፋኦ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል 138 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አደርጋለሁ አለ

ድርጅቱ የገንዘብ ድጋፉን የሚያደርገው ለኢትዮጵያ፣ኬንያ እና ሶማሊያ ነው

በአፍሪካ ቀንድ ለተከታታይ ሶስት ዓመታት ዝናብ ባለመዝነቡ 25 ሚሊዮን ዜጎች የምግብ እጥረት ገጥሟቸዋል

ፋኦ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል 138 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ።

የዓለም ምግብ እና ግብርና ድርጅት ፋኦ በአፍሪካ ቀንድ የገጠመውን የድርቅ ጉዳት እና የረሃብን አደጋ ለመቀነስ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ባወጣው መግለጫ አስታውቃል።

እንደ ድርጅቱ መግለጫ ከሆነ በአፍሪካ ቀንድ ድርቅ ያጋጠመው ለተከታታይ ሶስት ዓመታ ዝናብ ባለመዝነቡ ሲሆን በተለይም በሶማሊያ፣ ኬንያ እና ኢትዮጵያ ያሉ አርብቶ አደሮችን እና በእርሻ ስራ በሚተዳደሩ አርሶ አደሮች ላይ ምግብ እጥረት እንዲያጋጥማቸው አድርጓል።

በዚህም መሰረት በሶስቱ ሀገራት ያሉ ከ25 ሚሊየን በላይ ህዝቦች በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ውስጥ አስቸኳይ የምግብ እጥረት እንደሚያስፈልጋቸው ፋኦ በቅድመ ማስጠንቀቂያ ሪፖርቱ አስታውቋል።

በድርቁ ክፉኛ ለተጎዱት ሶስቱ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በአፋጣኝ ድጋፍ ካልተደረገላቸው ከአለማችን ከባድ የምግብ እጥረት የሚከሰትበት አካባቢ ይሆናልም ብሏል ድርጅቱ በመግለጫው።

በመሆኑም በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ በድርቅ ለተጎዱ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ፈጣን የሆነ የውሃ፣ ምርጥ ዘር፣የእንስሳት መኖ፣ መድሃኒቶችን እና በገጠር አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች ገንዘብ ድጋፍ በመስጠት ላንዣበበባቸው የረሃብ አደጋ ልንደርስላቸው ይገባል ሲልም ፋኦ ገልጿል።

ፋኦ ድጋፉን ለተጎጂዎች ማድረስ ከቻለ በሶስቱ ሀገራት ያሉ አርብቶ አደሮች የወተት ምርታቸውን 90 ሚሊየን ሊትር ወተት እንዲያመርቱ እና አርሶ አደሮች በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ውስጥ እስከ 40 ሺህ ቶን ምግብ እንዲያመርቱ አደርጋለሁም ብሏል።

በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከዝናብ እጥረት ጋር ተያይዞ የድርቅ አደጋ ማጋጠሙ የሚታወቅ ሲሆን፤ በኢትዮጵያም በኦሮሚ ክልል ቦረና ዞን እና በሶማሌ ክልል ድርቅ መከሰቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በሳላፍነው ሳምንት ለአል ዐይን እንዳስታወቀው፤ በዝናብ እጥረት ምክንያት በክልሉ ካ 11 ዞኖች ውስጥ በዘጠኙ ድርቅ ተከስቷል።

በድርቁ ሳቢያ በዘጠኙ ዞን ውስጥ የሚገኙ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ገደማ ዜጎች ለጉዳት መዳረጋቸውን ያስታወቀው ክልሉ፤ 250 ሺህ ገደማ እንሰሳት መሞታቸውን መግለጹ ይታወሳል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top