ለአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከሁሉ ቀድመው ካሜሮን የገቡት ዋሊያዎች

2 Yrs Ago
ለአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከሁሉ ቀድመው ካሜሮን የገቡት ዋሊያዎች
|ዋሊያዎቹ

በኮሮናቫይረስ ምክንያት በአንድ ዓመት የዘገየው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አሁንም በወረርሽኙ ስጋት ውስጥ ሆኖ በመጪው ወር ጥር 01/2014 ዓ.ም ካሜሩን ውስጥ መካሄድ ይጀምራል።

በዚሁ ውድድር መሳተፋቸውን ያረጋገጡት ዋልያዎቹም ባለፈው ሳምንት እሁድ ከሁሉም የአፍሪካ አገራት ቀድመው ካሜሩን በመድረስ ዝግጅታቸውን ጀምረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ጌታነህ ከበደን ጨምሮ 25 ተጫዋቾች በቡድኑ ውስጥ የተካተቱ ሲሆን፣ ካፍ ካስቀመጠው ገደብ በተጨማሪ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሦስት ተጫዋቾች እንዲካተቱ ተደርጓ።

ታኅሣሥ 14/ 2014 ይፋ ከተደረገው የብሔራዊ ቡድኑ 25 ተጫዋቾች ዝርዝር ከዚህ ቀደም በተጠባባቂነት ተይዘው የነበሩት ሱራፌል ዳኛቸው፣ ፍሬው ጌታሁን እና ይሁን እንደሻው ብሔራዊ ቡድኑን ተቀላቅለው ዋሊያዎቹ 28 ተጫዋቾችን በመያዝ ወደ ካሜሩን አቅንተዋል።

የኢትዮጵያ የወንዶች ብሔራዊ ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈው ከ8 ዓመታት በፊት ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው ውድድር ላይ ነበር።

ባለፈው እሁድ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፍያ የተነሳው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ልዑክ በቀዳሚነት የካሜሩን ሁለተኛ ከተማ ወደሆነችው ዱዋላ ደርሶ ለአንድ ሰዓት ከቆየ በኋላ ወደ ዋና ከተማዋ ያውንዴ ደርሷል።

ብሔራዊ ቡድኑ ያውንዴ አየር ማረፊያ እንደደረሰ የኮቪድ-19 ምርመራን ያደረገ ሲሆን በመቀጠል ወደ ሆቴል ዴ ዴፕዩቴ አምርቶ ማረፊያውን ማድረጉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን መረጃ ያሳያል።

ብሔራዊ ቡድኑ እስካሁን ቀላል እና ጠንከር ያሉ አራት ልምምዶችን አከናውኗል።

በዋሊያዎቹ ከሁሉ ቀድመው ለምን ወደ ካሜሩን ሄዱ?

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን እንደሚሉት የመጀመሪያ እቅድ ተደርጎ የነበረው በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ አገራት መካከል በአንዱ ውስጥ ዝግጅት ለማድረግ ነበር።

"ከሳዑዲ አረቢያ እግር ኳስ ማኅበር ጋር ንግግሮች ነበሩ። እንዲያውም ሙሉ ወጪያችንን ሸፍነው እነሱ ጋር ሄደን እንድንዘጋጅ ተነጋግረን ነበር።"

ነገር ግን የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ተከትሎ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት የጉዞ እግዳዎችን ከጣለባቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ በመሆኗ ሀሳቡ ሳይሳካ እንደቀረ ኃላፊው ለቢቢሲ ገልጸዋል። የሳዑዲ አረቢያ እግር ኳስ ፌደሬሽንም ቢሆን በተፈጠረው ነገር ማዘኑን እንደገለጸና ይቅርታ እንደመጠየቀም ኃላፊው አመልክተዋል።

የመጀመሪያው እቅድ አለመሳካቱን ተከትሎ ደግሞ ፌደሬሽኑ ወደ ሁለተኛ እቅዱ ፊቱን ለማዞር ተገዷል። ይህም ደግሞ ወደ ምዕራብ አፍሪካ አገራት በመሄድ ልምምድ ማካሄድ ነበር። በስተመጨረሻም ወደ አዘጋጇ አገር ካሜሩን በመሄድ ልምምድ ለማድረግ ውሳኔ ላይ ተደርሷል።

በተጨማሪም ብሔራዊ ቡድኑ ቀድሞ ወደ ካሜሩን ማቅናቱ የአገሪቱን የአየር ጸባይ ለመልመድ ይእንደሚረዳ የገለጹት አቶ ባሕሩ፣ የአፍሪካ ዋንጫ ዘንድሮ እንዳይካሄድ ከተለያዩ ወገኖች ግፊት ይደረግ ስለነበረ ያን በመቃወም ውድድሩ በተያዘለት ጊዜ እንዲከናወን ኢትዮጵያ ያላትን ድጋፍ ለማሳየት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፊፋንና የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበርን ጨምሮ አንዳንድ የእግር ኳስ ማኅበራት የወረርሽኙን ስርጨት ተከትሎ የአፍሪካ ዋንጫ በዚህ ጊዜ መካሄድ የለበትም የሚል አስተያየት ሲሰጡ እንደነበር ዋና ፀሐፊው ተናግረዋል።

"እኛ ደግሞ የፓንአፍሪካኒዝም ጀማሪዎች እንዲሁም የካፍ መስራች እንደመሆናችን ይሄ ውድድር በተያዘለት ጊዜ በካሜሩን እንደሚካሄድ ማረጋገጫ ለመስጠትና ይህንን መልዕክት ለማስተላለፍ ነው ቀድመን ወደ ካሜሩን ለማቅናት የወሰንነው።"

ኦሚክሮን የተባለው አዲሱን የኮቪድ-19 ዝርያ በስፋት መሰራጨትን ተከትሎ በርካቶች ውድድሩ ላይካሄድ ይችላል በሚል ስጋታቸውን ቢገልጹም፣ የየካሜሩን መንግሥት እና የእግር ኳስ ማኅበሩ እንዲሁም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ግን ጨዋታው በወጣለት መረሃ ግብር መሠረት እንደሚከናወን አረጋግጠዋል።

ነገር ግን በካሜሩን በሚካሄደው የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ላይ መታደም የሚችሉት የኮቪድ-19 ክትባትን ሙሉ ለሙሉ የወሰዱ እና ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው የተረጋገጠ ደጋፊዎች ብቻ እንደሚሆኑ አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

ካሜሩን ቆይታና ዝግጅት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሁን የሚገኘው የፊፋ ወኪል በሆነ ኤጀንት አማካይነት በተመቻቸ የስልጠና ካምፕ አገልግሎት መስጫ ውስጥ ነው። ይህ የስልጠና አገልግሎት መስጫ ካምፕ ሆቴል፣ መስተንግዶ፣ የስልጠና ቦታና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ሁሉ ያሟላ እንደሆነ አቶ ባህሩ ይገልጻሉ።

"አሁን ብሔራዊ ቡድኑ ያለበት ቦታ ሁሉንም ፍላጎታቸውን የሚያሟላ ነው። አሁን ላይም ተጫዋቾቹ አስፈላጊውን ስልጠናና ዝግጅት በዚህ ማዕከል እያደረጉ ነው'' ሲሉ ዋሊያዎቹ ለውድድሩ አስፋለጊውን ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ዝግጅት ያውንዴ ከከተመ ሳምንት ሊሆነው ተቃርቧል። በቆይታውም መደበኛ ልምምድ በማድረግ ከሳምንት ለሚጀመረው ውድድር እየተዘጋጀ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ከዋሊያዎቹ ቀጥሎ ካሜሩን ከደረሰው የሱዳን ብሔራዊ ቡድን ጋር ሐሙስ ዕለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርጓል።

በምድብ 'መ' ከግብፅ፣ ከናይጄሪያ እና ከጊኒ ቢሳዎ ጋር ከተደለደለችው ሱዳን ጋር በተደረገው የአቋም መለኪያ ጨዋታው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ሁለት፣ ሽመልስ በቀለ ደግሞ አንድ ግቦችን አስቆጥረው ዋሊያዎቹ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ለማሸነፍ ችለዋል።

ዋሊያዎቹ በካሜሩን በሚኖራቸው ቆይታ አጠቃላይ ወጪያቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ገንዘብ መድቦ እንደሚሸፍን የፌደሬሽኑ ዋና ፀሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የአፍሪካ አህጉር ትንቁ የእግር ኳስ ውድድር በሆነው ጨዋታ ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ ለሚቀርበው ቡድን የሚያስፈልገውን ገንዘብ ፌዴሬሽኑ ከመንግሥት አግኝቷል።

"ለዚህ ውድድር 51 ሚሊየን ብር እንዲመድብ ጠይቀን 35 ሚሊየን ብር ጸድቆልናል። በዚህ ገንዘብ ነው ብሔራዊ ቡድኑ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው። በዚህ አጋጣሚ መንግሥት ላደረገው ነገር በሙሉ ፌዴሬሽኑ ያመስግናል'' ብለዋል አቶ ባሕሩ።

ከዋሊያዎቹ ምን እንጠብቅ?

የአፍሪካ እግር ኳስ ውድድር መስራች የሆነችው ኢትዮጵያ ከውድድሩ ርቃ ከመቆየቷ በተጨማሪ ከአንድ ጊዜ በላይ የጎላ ውጤትን ሳታስመዘገብ ቆይታለች። በዚህ 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚሳታፈው ቡድን ግን ይህንን ታሪክ የመቀየር ከፍ ያለ ፍላጎት አለው።

ለዚህም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ዋሊያዎቹ በምድብ ጨዋታዎች ጥሩ ውጤት አስመዝግበው ከምድባቸው ማለፍን በቀዳሚነት የሚጠበቅ ውጤት እንደሆነ አቶ ባህሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ አንድ ከአዘጋጇ ካሜሩን፣ ከቡርኪና ፋሶ እና ኬፕ ቬርድ ጋር ተደልድሏል።

በዚህ ሂደትም ዋሊያዎቹ ከምድባቸው ወደቀጣይ ዙር ማለፍን የመጀመሪያ ግብ ከመሆኑ ጎን ለጎን "በስፖርት ዲፐሎማሲው ዘርም ሌሎች ኃላፊነቶችን እንመዲወስዱም" አቶ ባሕሩ ጠቅሰው "ኢትዮጵያን ለዓለም ሕዝብ በደንብ ማስተዋወቅና ማሳየት እንፈልጋለን። በዚህ ትልቅ አጋጣሚ አንድነታችንን ለመላው ዓለም በደንብ አድርገን እናሳያለን" ብለዋል።

በተጨማሪም ካሜሩን ውስጥ 20 የሚደርሱ የኢትዮጵያውያን ስብስቦች እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ባህሩ እነዚህን ኢትዮጵያውያን በማሰባብ ለብሔራዊ ቡድኑ ድጋፍ እንዲያደርጉ፣ እንዲሁም ከ500 በላይ የሚሆኑ ደጋፊዎች ከኢትዮጵያ ወደ ካሜሩን ለመጓዝ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top