የሰሞኑ ጉንፋን መሰል ህመም የኮሮናቫይረስ ሊሆን ስለሚችል ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ ተመከረ

04/01/2022 12:58
የሰሞኑ ጉንፋን መሰል ህመም የኮሮናቫይረስ ሊሆን ስለሚችል ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ ተመከረ

 በኢትዮጵያ አዲስ የኮሮናቫይረስ ማዕበል በመከሰቱ ሰሞኑን የተስተዋለው ጉንፋን መሰል ህመም የሚያሳው ምልክት ከኮሮናቫይረስ ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ህመሙ ያላባቸው ሰዎች ምርመራ እንዲያደርጉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መከረ።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም ባለፉት ሳምንታት በኢትዮጵያ ውስጥ የታየው በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር በአገሪቱ አዲስ የወረርሽኙ ማዕበል መከሰቱን እንደሚያሳይ ተቋሙ ገልጿል።

ሰሞኑን የተከሰተውን 'ጉንፋን መሰል' ወረርሽኝን በማስመልከት መግለጫ ያወጣው ተቋሙ እንዳለው በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአዲስ አበባ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ባደረገው የመስክ ቅኝትና የናሙናዎች ምርመራ ከ59 እስከ 86 በመቶው ላይ ኮቪድ-19 እንደተገኘባቸው አመልክቷል።

ጨምሮም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በጤና ተቋማት የኮሮናቫይረስ ምርመራ ካደረጉ 55 ሺህ 562 ሰዎች ውስጥ 25 ሺህ 191 ያህሉ ላይ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው መረጋገጡን ገልጿል።

እንዲሁም በመላው አገሪቱ ከታኅሣሥ 15 እስከ 21/2014 ዓ.ም ድረስ ባሉት ሰባት ቀናት ውስጥ የኮቪድ ምልክት ታይቶባቸው ምርመራ ካደረጉ 83 ሺህ 237 ሰዎች ውስጥ 29 ሺህ 279 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ተገኝተዋል።

ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ያለው በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ምጣኔ ተከታታይ ጭማሪ አሳይቷል።

በዚህም መሠረት ከሁለት ሳምንት በፊት የነበረው የ5 በመቶ ምጣኔ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቶ ሐሙስ (ታኅሣሥ 21/2014 ዓ.ም) ላይ ወደ 36 በመቶ ከፍ ማለቱን ተቋሙ አመልክቷል።

በዚህም ሳቢያ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዳለው እየታየ ያለው የወረርሽኙ መስፋፋት በአገሪቱ አዲስ የኮቪድ-19 ማዕበል መከሰቱን እንደሚያመለክት ገልጿል።

ተቋሙ ጨምሮም ሰሞኑን ከሚስተዋለው "ጉንፋን መሰል" ህመም ጋር የሚታዩት ምልክቶች ከኮቪድ-19 ምልክቶች ጋር ተመሳሳይ በመሆናቸው ሳይዘናጉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ መመርመር እንደሚገባ መክሯል።

በአሁኑ ወቅት የኮሮናቫይረስ ስርጭት በዓለም ዙሪያ በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ በመሆኑ ይህ ክስተት ኢትዮጵያ ውስጥም መስተዋሉን በመግለጽ ምልክቶች የታዩባቸው ሰዎች ምርመራ እንዲያደርጉ መክሯል።

የተቀረው ሕብረተሰብም የኮሮናቫይረስ መከላከያ መንገዶችን በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ እራሱንና ሌሎችን ከወረርሽኑ እንዲጠብቅ መክሯል።

የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ መኖሩ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ አስከ ሐሙስ ታኅሣሥ 21/2014 ዓ.ም ድረስ ከ4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተመርምረው ከ415 ሺህ በላይ ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን፣ 6 ሺህ 926 ደግሞ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን አጥተዋል።

በሽታውን ለመከላከል የሚረዳው ክትባት በአገሪቱ መሰጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የተከተቡ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ካላት አጠቃላይ ሕዝብ አንጻር ይህ አሃዝ ዝቅተኛ እንደሆነ ይነገራል።

የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር የተለመዱትን የመከላከያ ዘዴዎች በአግባቡ ዘወትር ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ባለሙያዎች እየመከሩ ሲሆን ክትባት መውሰድም እንደሚገባ ያሳስባሉ።

 

ግብረመልስ
Top