ወላዶች፤ የሚመገቡት በማጣታቸው ለማጥባት መቸገራቸውን የሰሜን ወሎ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ

2 Yrs Ago
ወላዶች፤ የሚመገቡት በማጣታቸው ለማጥባት መቸገራቸውን የሰሜን ወሎ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ

ወላዶች፤ የሚመገቡት በማጣታቸው ለማጥባት መቸገራቸውን የሰሜን ወሎ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ

ከፍተኛ የምግብ እና የመድኃኒቶች እጥረት እንዳጋጠማቸውም ነው ለአል ዐይን አማርኛ የተናገሩት

ነዋሪዎቹ ከወረራ ነጻ ብንወጣም ለከፋ ችግር ተዳርገናል ብለዋል

በቅርቡ በኢትዮጵያ ጥምር ጦር ነጻ በወጡ የአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን አካባቢዎች ከፍተኛ የምግብና የመድሃኒት እጥረት መኖሩን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ነዋሪዎቹ ሸቀጦች ወደ አካባቢዎቹ እየገቡ ባለመሆኑ ለከፋ ችግር መዳረጋቸውንና አካባቢዎቹ ነጻ ቢወጡም ችግሩ ግን ተባብሶ መቀጠሉን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን መርሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑና ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ ነዋሪ በከተማዋ የሸቀጥ መደብሮችን ጨምሮ ሌሎች ሱቆች እንዳልተከፈቱ፤ ‘ፓራሲታሞል’ን መሰል ማስታገሻ መድሃኒቶችን እንኳን በቀላሉ እንደማይገኙ እና በውድ ዋጋ እየተገዙ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በህወሓት ታጣቂዎች የተደፈሩ ሴቶች መደፈራቸውን “ሰው ሰማብን” በሚል ይሉኝታ ተይዘው ከቤት እየወጡ እንዳልሆነና ይህንኑ በመፍራት ቀያቸውን ለቀው እየሄዱ መሆኑንም ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በመርሳ የወንዝ ውሃ ነው እየተጠጣ ያለው እንደ ነዋሪው ገለጻ፡፡ 20 ሊትር የወንዝ ውሃ 50 ብር እየገዛን እንጠጣለንም ብለዋል፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች አካባቢያቸው ነፃ በመውጣቱ ቢደሰቱም መኖሪያ ቤቶቻቸውን ጨምሮ የከተሞቻቸው መውደም እጅግ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡ “የሚበላም ሆነ የሚጠጣ ነገር” እንደሌላቸውም ነው የገለጹት፡፡

የቆቦ ከተማ ነዋሪ የሆነው አቶ ጌታቸው ሕዝቡ ነጻነቱን ቢያገኝም አሁን ላይ ሸቀጥም ሆነ ቤንዚን እንደሌለና እንደተወደደ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጿል፡፡ በቆቦና አካባቢው ከ 7 እስከ 10 ኪሎ ሜትር ለሚሆን መንገድ እስከ 50 ብር የሚሆን ዋጋ እየተከፈለ እንደሆነ የገለጸው አቶ ጌታቸው የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ከመውደማቸውም በላይ ረዘም ላለ ጊዜ የሚወሰዱ መድሃኒቶች በመታጣታቸው ብዙዎች ለህይወት በሚያሰጋ ችግር ላይ መውደቃቸውንም አንስቷል፡፡

በወልዲያ እና በአካባቢው ተመሳሳይ ችግሮች ማጋጠማቸውንም ነው ነዋሪዎቹ የሚናገሩት፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ወሎ፣ የደቡብ ወሎ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ያደረጉትን ደጋግመው የሚያነሱት ነዋሪዎቹ “ብጹዕ አባታችን በመበደር ጭምር ነው ህይወታችንን ያቆዩት” ሲሉ ይናገራሉ፡፡

የወልዲያ አማራ ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ኤፍሬም አሰፋ አቡነ ኤርሚያስ ከቤተ ክርስቲያንና ከግለሰቦች በመበደር ያኖሯቸው የነበሩ ግለሰቦች አሁን ላይ ስራ ባለመኖሩና ድጋፍ በመታጣቱ ችግር ላይ ወድቀዋል ብሏል፡፡

ወላድ እናቶች በምግብ እጦት ምክንያት ለማጥባት ተቸግረዋል ያለም ሲሆን የንግድ እንቅስቃሴዎች በመቆማቸው ምክንያት ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ጭምር መቸገራቸውንና የቀን ስራ በመስራት ኑሯውን ይገፉ የነበሩ ዜጎች አሁን ስራ በመቆሙ ምክንያት ከነቤተሰቦቻቸው ለስቃይ መዳረጋቸውን ለአል ዐይን ተናግሯል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top