የሚኒስትሮች ምክር ቤት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

2 Yrs Ago
የሚኒስትሮች ምክር ቤት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባው በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።
 
መንግስት በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ይሁኝታ አግኝቶ ሲመረጥ ቃል ከገባባቸው አገራዊ ጉዳዮች መካከል ሁሉን አካታች የሆነ አገራዊ ምክክርና ውይይት በማካሄድ አገራዊ መግባባት እና በአገር ጉዳይ የጋራ አቋም እንዲኖር የሚያስችሉ ስራዎችን መስራት አንዱ መሆኑ ይታወቃል።
 
በዚሁ መሰረት መሠረታዊ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች በተለያየ ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ልሂቃንም ሆኑ ምልዓተ ህዝቡ ተቀራርቦና በአገራዊ አንድነት ገንቢ አቋም እንዲይዙ ለማድረግ አካታች አገራዊ ምክክሩን ተግባራዊ ለማድረግ በገለልተኝነት ለመምራትና ለማስተባበር የሚችል ቅቡልነት ያለው ተቋም ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ለውሳኔ ቀርቧል።
 
ምክር ቤቱም በቀረበው የማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top