የታንዛኒያ ሆስፒታሎች ውስጥ የሚገኙ የኮሮናቫይረስ ሕሙማን ቁጥር ቀንሷል፦ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት

4 Yrs Ago 6044
የታንዛኒያ ሆስፒታሎች ውስጥ የሚገኙ የኮሮናቫይረስ ሕሙማን ቁጥር ቀንሷል፦ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት



የታንዛኒያው ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ በሀገሪቱ ሆስፒታሎች ውስጥ የሚገኙ የኮሮናቫይረስ ሕሙማን ቁጥር በእጅጉ መቀነሱን ተናገሩ።

ፕሬዚዳንት ማጉፉሊ ይህን ያሉት በሀገራቸው የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በርካታ ሆስፒታሎች በሕሙማን ተጨናንቀዋል የሚል ሪፖርት ማውጣቱን ተከትሎ ነው።

በአንድ ወቅት 198 የኮሮናቫይረስ ሕሙማንን ሲያስተናግድ የነበረው የዳር ኤስ ሳላም ሆስፒታል አሁን ላይ 12 ቫይረሱ ያለባቸው ሕሙማንን ብቻ እያስተናገደ መሆነን ፕሬዘዳንቱ በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

ሌሎች ሆስፒታሎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ነው የገለጹት።

የትውልድ ስፍራቸው በሆነችው ቻቶ ከተማ በሚገኝ የአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተገኙት ፕሬዚዳንት ማጉፉሊ፣ የእርሳቸው ልጅም በቫይረሱ ተይዞ እንደነበር እና አሁን ግን መዳኑን ተናግረዋል።

"ፈጣሪ ጸሎታችሁን ሰምቷችኋል" በማለትም በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ገልጸውላቸዋል።

ታንዛኒያ ከኮሮናቫይረስ ሥርጭት ጋር በተያያዘ እንደሌሎች ሀገራት ጥብቅ የእንቅስቃሴ እገዳዎችን ያልጣለች ቢሆንም በርካታ ሰዎች የሚገኙበት ስብሰባዎች እንዳይኖሩ እና ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ አድርጋለች።

ይሁን እንጂ ሀገሪቱ ውስጥ በምሽት የሚፈፀሙ የቀብር ሥነ-ሥርዓቶች መኖራቸውን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በየማኅበራዊ ሚዲያው ሲሠራጭ ቆይቷል፤ ይህም መንግሥት ለኮሮናቫይረስ እየሰጠ ያለውን ትኩረት ጥያቄ ውስጥ አስገብቷል።

የሀገሪቱ ባለሥልጣናትም ከኮራናቫይረስ ሥርጭት ጋር በተያያዘ ኦፊሴላዊ መረጃዎችን ይፋ በማድረጉ ረገድ መዘግየት ይታይባቸዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት የታንዛኒያ መንግሥት እየተከተለ ባለው ስልት ላይ ያለውን ስጋት ገልጿል።

ፕሬዚንዳንት ማጉፉሊ አሁን ታይቷል ያሉት የሕሙማን ቁጥር መቀነስ በመጪው ሳምንትም በዚሁ ከቀጠለ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለመክፈት ማቀዳቸውን ይፋ አድርገዋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top