ኢትዮጵያ ለህዳሴ ግድቡ ድርድር ወደ አሜሪካ አሸማጋይነት እንደማትመለስ አስታወቀች

3 Yrs Ago
ኢትዮጵያ ለህዳሴ ግድቡ ድርድር ወደ አሜሪካ አሸማጋይነት እንደማትመለስ አስታወቀች

የህዳሴ ግድብ የውኃ አሞላልና አለቃቀን በተመለከተ በአሜሪካ አሸማጋይነት ሲካሄድ ቆይቶ ያለ ስምምነት ወደ ተቋረጠው መድረክ እንደማትመለስ፣ ኢትዮጵያ በይፋ አስታወቀች።

ይህ የተገለጸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ሰኞ ግንቦት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰበሰቡት የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብሔራዊ ምክር ቤት፣ የግድቡን የግንባታ ደረጃና ከዚህ ጋር የተያያዙ አጠቃላይ ፖለታካዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ በተረደገው ውይይት ነው።

ይህንን ውይይት አስመልክቶ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፣ በአሜሪካና በዓለም ባንክ ታዛቢነት በግድቡ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል ሲደረግ የቆየው ድርድር ወደ ስምምነት የማያደርስ በመሆኑ እንደተቋረጠ መቅረቱን ገልጸዋል።

‹‹በአሜሪካ ሲካሄድ የነበረውን የውይይት ሒደት ከተውነው ሰነባብተናል፤›› ሲሉ፣ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ሚኒስትሩ በይፋ አስታውቀዋል። በቀጣይ ሊኖር የሚችለው ድርድሩ በሚመለከታቸው ሦስቱ አገሮች መካከል ብቻ እንደሚሆን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ይህም የሚሆነው ሦስቱም አገሮች ተስማምተው በሚቀበሉት አሸማጋይ ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል።

አሸማጋይ የማስገባት ጉዳይ አስፈላጊ ከሆነ ኢትዮጵያ እንደ ቀድሞው ወደ አሜሪካ መንግሥት የመሄድ ፍላጎትን እንደማትቀበል አስረድተዋል። የተሻለ አሸማጋይ ከአፍሪካ ሊመረጥ ይችላል ብለው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ፍላጎትም ወደ አፍሪካ መመለስ እንደሆነ አመልክተዋል።

‹‹ለእኛ ዋናው ውጤት የግድቡን ግንባታ በትኩረት በማከናወን በዕቅዱ መሠረት፣ በመጪው ሐምሌ ወር በግድቡ ውኃ መሙላትና ቀሪ ግንባታውንም  ማጠናቀቅ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የግድቡ የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ በታችኞቹ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት ሳያደርስ እንደሚከናወን ያመለከቱት ሚኒስትሩ፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ የታችኞቹ አገሮች በተለይም በግብፅ መንግሥት በኩል ለሚነሳው ጥያቄ መፍትሔው ውይይት ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል። ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በየትኛውም ደረጃ ለሚነሱ ክርክሮች ዝግጁ መሆኗንም አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሩት በዚህ ውይይት ፕሮጀክቱ የደረሰበትን ደረጃ ግምገማ፣ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያና ለሁለቱ የታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች፣ እንዲሁም ለአካባቢው ሊያበረክት ስለሚችላቸው ጥቅሞች ገለጻና ውይይት ተደርጓል።

የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅን በተመለከተ በሦስቱ አገሮች መካከል ስላለው ድርድርና መፍትሔዎችም ጭምር ውይይት ተካሂዶ አቋም መያዙን ሚኒስትሩ አመልክተዋል። ኢትዮጵያ በግድቡ የመጀመሪያውን ዙር የውኃ ሙሌት በመጪው ሐምሌ 2012 ዓ.ም. ለመጀመር የወሰነች ሲሆን፣ ሰሞኑን በተካሄደው ስብሰባም መንግሥት በዚሁ አቋም መፅናቱ ታውቋል።

የግብፅ መንግሥት ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን የመጀመርያ ዙር የውኃ ሙሌት በሐምሌ ወር ልትጀምር አይገባም ሲል አቤቱታውን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ያቀረበ ሲሆን፣ ይህንንም በተመለከተ በሰሞኑ ብሔራዊ ስብሰባ ውይይት እንደተደረገበት ታውቋል።

የግብፅ መንግሥት ለተመድ ያቀረበው አቤቱታ ኢትዮጵያ የመልማትና የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም ሉዓላዊ መብት ያላት መሆኑን ያላገናዘበ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በማንኛውም ወገን ጫና ኢትዮጵያ ይህንን ሉዓላዊ መብቷን ልታጣ ወይም ልትተው እንደማትችል አስታውቀዋል።

የቀረበው አቤቱታ በቀጥታ ለኢትዮጵያ መንግሥት ግልባጭ ባይደረግም፣ በአቤቱታው ለተነሱ ጉዳዮች መልስ ለመስጠት ኢትዮጵያ በዚህ ሳምንት ለተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ደብዳቤ እንደምትልክ ታውቋል።

ሚኒስትሩ ለሚዲያዎች በሰጡት ማብራሪያ፣ ኢትዮጵያ የግድቡ የውኃ ሙሌትን በተመለከተ በሦስቱ አገሮች መካከል ድርድር እንዲደረግ አሁንም ፈቃደኛ እንደሆነች ተናግረዋል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከተያዙት አማራጮች መካከል በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የሚካሄደውን የመጀመርያ ዙር የውኃ ሙሌት ሥነ ሥርዓት አስመልክቶ፣ በኢትዮጵያ የተሰናዳ የድርድር ሰነድ ለሁለቱ አገሮች ለመላክ በቀዳሚ አማራጭነት መቀመጡን ገልጸዋል።

አጠቃላይ የግድቡን የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ በተመለከተ በሒደት ድርድር እንዲደረግበት፣ በቀዳሚ አማራጭነት መያዙን አመልክተዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top