በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስምንት ወራት ለ1ሺህ 547 ባለሐብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታውቋል።
በአማራ ክልል ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች በመጠቀም የሚያለሙ ባለሐብቶች ቁጥር እያደገ መምጣቱን የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዮሐንስ አማረ ተናግረዋል።
ክልሉን የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረግ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ የኢንቨስትመንት አማራጮች የመለየት፣ የማደራጀትና በተለያየ መንገድ ለባለሐብቱ የማስተዋወቅ እንዲሁም አሰራሮችን የማሻሻል ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በተከናወነው ጠንካራ ስራም ባለፉት ስምንት ወራት ከ294ሺህ 690 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ ለ1ሺህ 547 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ነው የተናገሩት።
የኢንቨስትመንት ፍቃዱም ከ251 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሐብቶች መሰጠቱን ገልጸው፤ ይህም የክልሉ ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱ የኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲያድግ እድል መፍጠር ማስቻሉን አንስተዋል።
ለባለሃብቶች እየተሰጠ ያለው የቅርብ እገዛ መሻሻሉን አመልክተው፤ባለፉት ወራት 286 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የነበረባቸውን ችግሮች በመፍታት ወደ ማምረትና አገልግሎት እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል።
የመሬት አቅርቦት እጥረት ለነበረባቸው ፕሮጀክቶች 429 ሄክታር መሬት ማስተላለፍ እንደተቻለ ጠቅሰው፤ በተለይም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተሻለ አቅምና ልምድ ያላቸው ባለሃብቶች ወደ ክልሉ መጥተው በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ማድረጉን አብራርተዋል።
እንዲሁም ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የባለሃብቶችን የመንገድ፣ የውሃ፣ የሃይል አቅርቦት፣ የብድርና መሰል ችግሮችን መፍታት መቻሉን ተናግረዋል።
በክልሉ ያለውን የተሻለ ሰላም በመጠቀምም 509 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችም ወደ ግንባታና በቅድመ ግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ አቶ ዮሐንስ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በቀጣይም ባለሃብቶችን በቅርበት በማገዝ በግብርና፣ ሆርቲካልቸርና መሰል ዘርፎች በስፋት እንዲሰማሩ ተገቢው እገዛና ድጋፍ እንደሚደረግ አብራርተዋል።