# ኢኮኖሚን በተመለከተ
ባለፉት ስምንት ወራት በዋና ዋና የኢኮኖሚ አመላካቾች ታላላቅ ስኬቶች ተመዝግበዋል። በቀጣይ የበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት ይህን ስኬት ማጠናከር ከተቻለ ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት ከ8 ነጥብ 4 በመቶ በላይ የኢኮኖሚ እድገት ታስመዘግባለች።
# ግብርናን በተመለከተ
በግብርና ምርት የአነስተኛ አርሶ አደሮች የሰብል ሽፋን 20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ደርሷል። በስንዴ ልማትም በመኸር 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር እንዲሁም በበጋ መስኖ ልማት 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ የተሸፈነ ሲሆን፤ በዚህም ከ300 ሚሊየን ኩንታል ያላነሰ ምርት ይስበሰባል ተብሎ ይጠበቃል። በቡና እና ሻይ ምርትም የተሻለ ስኬት እየተመዘገበ ነው። ለአብነትም ባለፉት ስምት ወራት ብቻ ከቡና ወጪ ንግድ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።
# ኢንዱስትሪን በተመለከተ
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ስትሪንግ ኮሚቴ ተቋቁሞ በኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ ያሉ ማነቆዎችን የመፍታት ስራ ሲከናወን ቆይቷል።በዚህም የውጭ ምንዛሬ፣ የኃይል አቅርቦትና ሌሎች ችግሮች የተለዩ ሲሆን ችግሮቹን ለመቅረፍም እየተሰራ ነው።
ለአብነትም በዘንድሮው ዓመት ብቻ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ የቀረበው የኃይል አቅርቦት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር የ50 በመቶ ብልጫ አለው። ከጥቂት ዓመት በፊት የአቅርቦት ጥያቄ የነበረበት የሲሚንቶ ምርትም አሁን ላይ ለውጭ ገበያ ጭምር ማቅረብ የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው።የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 61 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ብቻ 55 አዳዲስ ፋብሪካዎች ስራ ጀምረዋል።
# አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ
መንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ሁለት ዋና ዋና ስራዎች መከናወን አለባቸው። አንደኛው በቀበሌ ደረጃ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ሲሆን፤ እያንዳንዱ ቀበሌ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የሚያስችሉ አቅሞችን መገንባት ነው። በዚህም ሁሉም ቀበሌዎች ያላቸውን ሃብት በቁጥር ለይተው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው። ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ሁለተኛው መሶብ የተሰኘ አገልግሎት ሲሆን በሙከራ ደረጃ በሲቪል ሰርቪስና በፕላንና ልማት ሚኒስትር በሲስተም ይጀመራል። አገልግሎቱም በአንድ መስኮት ሁሉንም አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው።
# ገቢን በተመለከተ
ባለፉት ስምንት ወራት 580 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል። ነገር ግን መንግስት የሚሰበስበው ገቢ ከጥቅል ሀገራዊ ምርት አንጻር ከ7 በመቶ አይበልጥም። ይህን ማሻሻል አለብን። በየአከባቢው የሚቀርቡ የልማት ጥያቄዎችን መመለስ የምንችለው ገቢያችንን በበቂ ሁኔታ ማሳደግ ስንችል ብቻ ነው።
# የዋጋ ንረትን በተመለከተ
መንግስት በከፍተኛ ሁኔታ ድጎማ በማድረግ የዋጋ ንረቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች እንዳይጎዳ በጥንቃቄ እየሰራ ነው። ለአብነትም መንግስት በአንድ ኩንታል ማዳበሪያ 3 ሺህ 700 ብር ይደጉማል። ለነዳጅም 72 ቢሊዮን ብር ተደጉሟል። በዚህም በሊትር 28 ብር እንደጉማለን። የደሞዝ ጭማሪ በማድርግም ቋሚ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ገቢያቸው እንዲያድግ እየተሰራ ነው። ይህ ስራም ተጠናክሮ ይቀጥላል።
# የአፈር ማዳበሪያን በተመለከተ
እንደ ህዳሴ ግድብ ሁሉ የኢትዮጵያ ቀጣዩ ታላቅ ስራ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ነው። ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ ማምረት መጀመር አለብን ብለን ስራ ጀምረናል።ይህን ስራም በተለይ ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተሳሰር ለመስራት እየተጋን ነው። አሁን ላይ ግን ኢትዮጵያ በየዓመቱ 24 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ የሚያስፈልጋት ሲሆን፤ ይህን ፍላጎት ለሟሟላትም በየቀኑ 150 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ እያጓጓዝን ነው።
# የኮሪደር ልማትን በተመለከተ
የኮሪደር ልማት ከዛሬ ባሻገር ቀጣዩ ትውልድን መሰረት ያደረገ ነው። በአዲስ አበባ ብቻ በኮሪደር ልማት አማካኝነት ከ200 ኪሎሜትር በላይ መንገድ ተሰርቷል። ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶችም ተከናውነዋል። በኮሪደር ልማቱ ለተነሱ ዜጎችም በቂ ካሳ ተከፍሏል። እስካሁን ባለው ሂደትም ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ ካሳ ተከፍሏል። በሁሉም የክልል ከተሞችም አስደማሚ ስራ እየተከናወነ ነው፤ ለአብነትም በሐረር ከተማ በዜጎች ተሳትፎ የተከናወነው ስራ ለሀሉም ከተሞች ምሳሌ የሚሆን ነው።
# የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህልን በተመለከተ
በኢትዮጵያ ሁለት መሰረታዊ ስብራቶች አሉ፤ አንደኛው የመጠፋፋት ባህል ነው። መንግስታት ወደ ኃላፊነት ሲመጡ ሳይደራጁ ለማጥፋት የሚደረግ ሙከራ ማለት ነው። ይህ በበርካታ የኢትዮጵያ መንግስታት ታሪክ ተሞክሯል። ሁለተኛው ከሶሻሊስት እሳቤ ጋር በስፋት ወደ ኢትዮጵያ የገባው በሽታ ነው። ይህ በኢትዮጵያ ያመጣው ችግር ፍረጃ ነው። የጠላትና የወዳጅ ፍረጃ ማለት ነው። ይህም ለሰላማዊ ድርድር ቦታ አይሰጥም። ይህም በኃይል ስልጣን የመያዝ አባዜን አምጥቷል።ኢትዮጵያ ውስጥ እየተስተዋለ ያለውም ችግር ይህ ነው።በምርጫ የተመረጠን መንግስት በኃይል ለመጣል የሚሞክሩ ኃይሎች አሉ። የሚገርመው ነገር ግን የሚያሰቃዩት እንታገልልሃለን የሚሉትን ህዝብ ነው።
# ሰላምን በተመለከተ
መንግስት ለትችት ክፍት ነው። በሚያነሳው ሃሳብ ምክንያት የታሰረ አንድም ሰው የለም። ነገር ግን በአንድ እጅ ሰላማዊ ትግል፤ በሌላ እጅ በጦርነት መንግስት ለመጣል የሚሞክሩ ኃይሎች አሉ። ይህ ህግን መጣስ ነው። ነጻነትን በአግባቡ የማስተዳደር ችግር አለ። ነገር ግን መንግስት አሁንም ለሰላም ጽኑ አቋም አለው። ችግሮች በድርድር እንዲፈቱ ነው የምንሻው ። ባለፉት 7 ዓመታት ከየትኛውም የጎረቤት ሀገራት ጋር ጦርነት ያላካሄደ መንግስት አሁን ያለው መንግስት ነው። ይህም ከሀገር ባለፈ ለቀጣናው ሰላም ያለንን አቋም የሚያሳይ ነው።
# የፕሪቶሪያ ስምምነትን በተመለከተ
የፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረተ ልማቶችን በመመለስ የትግራይ ህዝብ አገልግሎት እንዲያገኝ አድርጓል። ያም ሆኖ አሁንም በበቂ ሁኔታ ያልተፈጸሙ ጉዳዮች አሉ። ከዚህም አንደኛው የታጣቂዎች ተሃድሶ (ዲዲአር) ስራ ነው። ይህ በዋናነት የሚጎዳው የትግራይ ህዝብን ነው። ወጣቶች በታጣቂ ስም ከመቀመጥ ወደ ልማት መሰማራት አለባቸው። በየወሩ ለልማት መዋል የነበረበት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለዚህ ስራ ይወጣል።
ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በመመለስ ረገድም በራያና ጸለምት ጥሩ ስራ ተከናውኗል። በሌሎች አከባቢዎች ግን በተፈለገው ልክ አልሆነም። ይህ የሆነውም ሰብዓዊ ስራ እና ፖለቲካ የሚቀላቅሉ ኃይሎች በመኖራቸው ነው። ነገር ግን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለፉት ሁለት ዓመታት ተጨማሪ ጦርነትን በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ ስራ አከናውነዋል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተሰጠው የሁለት ዓመት ጊዜ በማለቁ የህግ ማሻሻያ የሚፈልግ ጉዳይ አለ።ህግ ሲሻሻል ደግሞ የነበሩ አፈጻጸሞች መገምገም አለባቸው። በዚህም የፕሪቶሪያውን ስምምነት ባከበረ መልኩ መጠነኛ ለውጥ ከተካሄደ በኋላ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስራውን እያከናወነ ህዝቡን ለምርጫ የሚያዘጋጅ ይሆናል። ይህን በተመለከተም ከጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች እየተደረጉ ነው። በዚህ ሂደት ስራዎች ተገምግመው የግለሰቦች መቀያየር ሊኖር ይችላል።
#PMOEthiopia