ዓለም አቀፍ የዲጂታል ትምህርት ቀን

8 Hrs Ago 115
ዓለም አቀፍ የዲጂታል ትምህርት ቀን

ዛሬ ዓለም አቀፍ የዲጂታል ትምህርት ቀን በመላው ዓለም ተከብሮ ውሏል።

በፈረንጆቹ 2019 መጨረሻ ላይ ተከስቶ የነበረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመላው ዓለም ካስከተላቸው በርካታ ጉዳቶች መካከል በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የፈጠረው መስተጓጎል አንዱ ነበር።

ወረርሽኙ በመደበኛው የትምህርት ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ በመፍጠር ከማስተጓጎሉም ባሻገር የትምህርት ተደራሽነት ላይ ያሉ ልዩነቶችንም አጉልቶ አሳይቷል።

ታዲያ በዚህ ቀውስ ውስጥ ነበር ዲጂታል ትምህርት በዓለም አቀፍ ደረጃ የትምህርትን መፃኢ ጊዜ በመቅረጽ ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳለው እውቅና ያገኘው።

በወቅቱ በወረርሽኙ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት የዲጂታል ዓለም ተፈጥሮ ተማሪዎች በየቤታቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ተደርጓል።

የተመድ የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አባል ሀገራትም በፈረንጆቹ 2023 መጋቢት 19 ቀን ዓለም አቀፍ የዲጂታል ትምህርት ቀን ሆኖ እንዲከበር አውጇዋል 

የዘንድሮ የዓለም አቀፍ የዲጂታል ትምህርት ቀን "የዲጂታል ትምህርትን በዝቅተኛ ሐብት እውን ማድረግ" በሚል መሪ ሀሳብ ነው የተከበረው።

የዲጂታል ትምህርት፣ የትምህርት ተደራሽነትን የማስፋት፣ የትምህርት ውጤቶችን የማጎልበት እና የ21ኛው ክፍለ ዘመን ውስብስብ ፈተናዎችን ለመቋቋም በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ትምህርትን የማስታጠቅ አቅም አለው።

በተለይም በግጭት እና በድንገተኛ አደጋዎች የተጎዱ ሰዎችን የሚያካትት እና የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ የሚያደርግ በመሆኑ የትምህርት ተደራሽነትን ለማጠናከር ጉልህ ሚና ይጫወታል።

በአሁኑ ወቅት የዲጂታል ክህሎቶች እና የሚዲያ እውቀት በእጅጉ አስፈላጊ በመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ የመሠረታዊ ትምህርት ዋና አካል እየሆኑ መጥተዋል፤ ምክንያቱም ያለእነዚህ እውቀቶች ማንም ሰው በማኅበራዊ፣ በሲቪክ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ውስጥ በብቃት እና በኃላፊነት ለመሳተፍ አይችልምና።

በዓለም ዙሪያ አዳዲስ ልማዶችን በመመርመር እና በማቀናጀት ለውጥ ለሚያደርጉ የትምህርት ዘዴዎች ላይም መሠረት ይጥላል።

ይሁን እንጂ የዲጂታል አቅርቦት እኩል አለመሆን በርካታ ተማሪዎች ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም እንዳያገኙ ዘላቂ እንቅፋት ስለሆነባቸው ይህ በአስቸኳይ ሊፈታ እንደሚገባ ነው የዩኔስኮ ዋና ዳይሬክተር ኦድሬይ ዘሉላይ የሚናገሩት።

ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች የግለሰቦችን አጠቃላይ ዕድገት ለመደገፍ ጥቅም ላይ መዋል እንዲሁም የማኅበረሰቦቻችንን አካታች እና ዘላቂ ልማትንም መቅረፅ እንዳለባቸው ነው ዋና ዳይሬክተሯ የገለጹት።

ሀገራችንም ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት በመስጠት የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ 2025 ተቀርፆ ወደ ሥራ ተገብቷል።

"የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዟችንን ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ እንደ ሀገር ወሳኝ ርምጃዎችን ተራምደናል" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት መናገራቸው ይታወሳል።

"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" ለፈጠራ ሰዎች ድጋፍ በማስገኘት እና ለዲጂታል ጉዞ አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር በዲጂታል ኢኮኖሚ እንድንበረታ አቅም ሆኖናልም ነበር ያሉት።

"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" አካል በሆነው የ5 ሚሊዮን ኮደሮች የሥልጠና መርሐ-ግብርም እስካሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ500 ሺህ በላይ ሠልጣኞች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ጥራት ያለው የዲጂታል ትምህርት ለተማሪዎች ለማድረስ በዲጂታል የትምህርት ሥርዓት ላይ ከሚሠራው “ለርኒንግ ሉፕ” ከተባለ ድርጅት ጋር ባለፈው ጥቅምት ወር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙም ይታወሳል።

የመማር ተደራሽነትን በዲጂታል መድረኮች ማሳደግ፣ ሀገራዊ የልማት ግቦችን መደገፍ እንዲሁም የሀገሪቱን ሥርዓተ ትምህርት የተከተሉ የዲጂታል የመማሪያ መፍትሔዎችን በማዘጋጀት ዘላቂ ዲጂታል ትምህርትን ማሳደግ በስምምነቱ በትኩረት የሚሠሩ ሥራዎች መሆናቸው ነበር የተገለጸው።

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚታገዝበት ሥርዓትንም እየዘረጋች ትገኛለች።

መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት ወጣቱ ተጠቃሚ የሚሆንባቸው ሥልጠናዎች መመቻቸታቸው በዘርፉ አመርቂ ውጤቶችን እንደሚያስገኝም ይታመናል።

በሜሮን ንብረት


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top