አዋጭ ለሆኑ አምራች ዘርፎች የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር የለም፡- ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)

10 Hrs Ago 78
አዋጭ ለሆኑ አምራች ዘርፎች የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር የለም፡- ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)
አዋጭ ለሆኑ የአምራች ዘርፍ ፕሮጀክቶች የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር አለመኖሩን የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
 
የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በኩል ከኅብረተሰቡ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
 
በኢትዮጵያ በአምራች ዘርፉ የተሰማሩና መሳተፍ የሚፈልጉ አካለት በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ስራቸውን መቀጠልም ሆነ ግንባታቸውን ማካሄድ አልቻሉም፤ መንግስት ጉዳዩን እንዴት ይመለከተዋል? በሚል ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
 
ሚኒስትሯ በምላሻቸው፣ በአምራች ዘርፉ የተሰማሩ ፋብሪካዎች የውጭ ምንዛሪ ስለፈለጉ ብቻ ምንዛሪውን ላያገኙ የሚችሉበት እድል መኖሩን ገልጸው፤ ባንኮች የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቱን አዋጭነት በመገምገም ሊወስኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
 
የውጭ ምንዛሪ እጥረት ብቻውን ፋብሪካዎችን ከመገንባት አያቆምም ያሉት ሚኒስትሯ፤ ኢንቨስትመንቱ አዋጭ ከሆነ የውጭ ምንዛሪ እና ብድር ከባንኮች ማግኘት እንደሚቻል ነው የገለጹት።
 
በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ትልቅ ማዋቅራዊ ችግር የነበረውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥር ነቀል በሆነ መንገድ እንዲፈታ አድርጎታል ነው ያሉት ሚኒስትሯ። በዚህም ባላፉት 7 ወራት የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እየተሻሻለ መምጣቱን ነው የተናገሩት።
 
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ 7 ወራት ለውጭ ገበያ የቀረበው የምርት መጠን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ102 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቅሰዋል።
 
ከውጭ ከተላከ ገንዘብ (ሬሚታንስ) የተገኘው የውጭ ምንዛሪ በ14 በመቶ ማደጉን ገልጸው፤ ከልማት አጋሮች ባለፉት ሰባት ወራት 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱንም አንስተዋል።
 
ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ባለፉት 6 ወራት ብቻ ሁለት ጊዜ በጨረታ የውጭ ምንዛሪ በማቅረቡ ባንኮች የ5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ግዢ መፈፀማቸውን ተናግረዋል።
 
ባንኮቹ ከገዙት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ውስጥ 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር መሸጣቸውን ጠቅሰው፤720 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ይገኛል ብለዋል።
 
በኢትዮጵያ ታምርት እንቅስቃሴ በተለያዩ ምክንያቶች ስራ አቁመው የነበሩ 395 ፋብሪካዎች ችግሮቻቸው ተፈትቶላቸው ዳግም ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል።
 
ለአምራች እንዱስትሪዎች የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ከአምናው የተሻለ አቅርቦት መኖሩን የተናገሩት ሚንስትሯ፤ የፋብሪካ ጥሬ ዕቃ ግብዓት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ20 በመቶ በላይ ጭማሪ ማሳየቱን ነው የጠቀሱት።
 
በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ እጥረት መዋቅራዊ ችግር የሚሆንበት ሁኔታ አለመኖሩን የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
 
በላሉ ኢታላ
 
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top