አሁን ላይ የተገነባው የትምህርት ሥርዓት ቀልዶ የሚታለፍበት እንዳልሆነ እየታወቀ ነው ሲሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ገለጹ። የትምህርት ሥርዓቱን ለማስተካከል የተለያዩ ሪፎርሞች መደረጋቸውንም አንስተዋል።
ትምህርት እውቀት የሚዳብርበት እና በትጋት ተሰርቶ ውጤት የሚገኝበት መሆኑ ቀርቶ በአቋራጭ ዲግሪ እና ዲፕሎማ የሚገኝበት እንደነበር የሚናገሩት ሚኒስትሩ፤ ይህንንም ለማስተካከል መንግስት የምዘና ስራዎችን እየሰራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የትምህርት ሥርዓቱን በመቀየር ደረጃ የተደረገው ሪፎርም ተማሪዎች በስነ-ምግባር የታነጹ እንዲሆን ለማስቻል እንደሆነም ጠቁመዋል። በዚህም ቀርተው የነበሩ የስብዕና መገንቢያ ትምህርቶች ድጋሚ እንዲካተቱ አድርገናል ብለዋል።
በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ሁሉም ዜጎች ጥሩ ትምህርት ማግኘት ይገባቸዋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የትምህርት ሪፎርሙ አንዱ እና ትልቁ ስራው በተቻለ መጠን ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ህጻናት ተመጣጣኝ የሆነ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲደርሳቸው ማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል።
የትምህርት ጥራት ችግር ከመሰረተ ልማት፣ ከመምህራን የማስተማር አቅም፣ ከሥርዓተ ትምህርቱ ጋር የተያያዘ በመሆኑ፤ በእነዚህ ዘርፎች ለውጥ ለማምጣት እየሰራን ነው ብለዋል። የትምህርት ቤቶችን ግንባታ በመልከአ ምድር አቀማመጥ ብቻ ሳይሆን፤ የተማሪዎችን ብዛት ያማከለ በሆነ መልኩ የመገንባት ሂደት መጀመሩንም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
የትምህርት ጥራቱን ለማሻሻል ከታች ያሉ ትምህርት ቤቶች ጋር ከፍተኛ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል። በመላ ሀገሪቱ በሚባል ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሞላ ጎደል 0 ክፍል ወይም የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ህጻናት ማግኘት ችለዋል ሲሉም ተናግረዋል።
በገጠሩም ሆነ በከተማ ያሉ ህጻናት የትምህርት የዝግጅት ዕድሜ እንዲኖራቸው ተደርጓልም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ የትምህርት ሥረዓት ላይ የጥራት ጉድለት ስለመኖሩም አንስተው ይህን ለማሻሻል ልዩ ትኩረት አድርገን እየሰራንበት እንገኛለን ብለዋል። ለዚህም ማሳያ የመምህራንን የማብቃት ስራ ዋነኛው በመሆኑ የመምህራንን ብቃት ለማረጋገጥ ስልጠናዎች እየተሰጡ ስለመሆኑም ነው የጠቀሱት።
የመምህራኖችን ምቾትም ለመጠበቅ የመኖሪያ ቤት ከመስጠት ጀምሮ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ስለመኖራቸው ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።