የተሻሉ እና ጠንካራ ሥራ ፈጣሪ ሴቶችን እናበቃለን፦ የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር

10 Hrs Ago 55
የተሻሉ እና ጠንካራ ሥራ ፈጣሪ ሴቶችን እናበቃለን፦ የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር
በተለያዩ ተግዳሮቶች ሳቢያ ወደ ኋላ የቀሩ እንዲሁም ዕድል የተነፈጉ ሴቶችን በማጠናከር የተሻሉ እና ጠንካራ እንዲሆኑ እናደርጋለን ስትል የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት በረከት ወርቁ (በረከት ገበሬዋ) ገልጻለች።
 
የሥራ ሐሳብ እያላቸው በገንዘብ፣ በእውቀት እና በሌሎችም ችግሮች ውስጥ ያሉ ሴቶችን በፋይናንስ፣ በሥልጠና እንዲሁም የልምድ ልውውጥ መድረክ ላይ የሚሳተፉበትን ዕድል በማመቻቸት ነጥረው እንዲወጡ ለማድረግ ሥራ መጀመሩን ነው ፕሬዚዳንቷ ለኢቢሲ ዶትስትሪም የተናገረችው።
 
በቅርቡ ማኅበሩን በፕሬዚዳንትነት የተረከበችው በረከት፣ የብሪክስ አባል የሆነችው ኢትዮጵያ ምርቶቿን ለማስተዋወቅ ይህን መሰል ማኅበራት ያስፈልጓታል ብላለች።
 
እንዲሁም ማኅበሩ የሀገራችን ሴቶች ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ የሚታይበት እና የሀገር ገፅታ የሚገነባበት መሆኑን አንስታለች።
 
ከተቋቋመ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረው ማኅበሩ፤ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዳልተወጣ ጠቁማ፣ ይህም ኅብረቱ መፍጠር የሚችለውን ለውጥ እና ተፅዕኖ እንዳያሳይ አድርጓል ብላለች።
 
ይህንኑ ለመቅረፍ እንደ አዲስ በተመሰረተው ማኅበሩ የቁሳቁስ፣ የአሠራር ብሎም የአመራር ለውጦችን በማድረግ ሴቶች ያሏቸውን ምርቶች እና የሥራ ፈጠራ ሐሳቦች ለሀገር ውስጥ እንዲሁም ለዓለም አቀፍ መድረክ ማቅረብ የሚችሉበት እንዲሆን በለውጥ ሂደት ላይ እንገኛለን ስትል ገልጻለች።
 
በዚህም በ30 ቀን ዕቅድ የኮሜሳ የንግድ ትርዒት ላይ 100 ሥራ ፈጣሪ ሴቶችን ተሳታፊ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ነው አያይዛ የጠቆመችው።
 
እንደ በረከት ገለጻ፣ ማኅበሩ ሴቶችን በብዙ መልክ ማገዝ፣ በፋይናንስ እና ሌሎችም ጉዳዮች ራሱን የቻለ ተቋም ማብቃት እና ለውጦችን ማፋጠን ዕቅዱ አድርጎ ሥራ ጀምሯል።
 
በአፎሚያ ክበበው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top