ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኋላ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ መጥቷል ፡- ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

16 Hrs Ago 49
ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኋላ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ መጥቷል ፡-  ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)
ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኋላ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ መምጣቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
 
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከህዝብ ለተነሱ ጥያቄዎች ሚኒስትሮች ምላሽ የሚሰጡበትን “እውነት ነው? ፤ ሐሰት?” የተሰኘ መድረክ አዘጋጅቷል፡፡
 
በመድረኩ ላይ ለገንዘብ ሚኒስቴር ከቀረቡ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ ፤ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኋላ የኑሮ ውድነት በሁለት እጥፍ ጨምሯል የሚል ይገኝበታል፡፡
 
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በምላሻቸው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የዋጋ ግሽበትን በመቀነስ እና ገበያን በማረጋጋት ረገድ ስኬታማ መሆኑን በመግለጽ ጥያቄው “ሐሰት” መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
ለአብነትም በየካቲት ወር የነበረው የዋጋ ግሽበት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ13 በመቶ እንደሚያንስም ጠቁመዋል፡፡
 
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ገበያን በማረጋጋት በኩል ተጨባጭ ውጤቶችን ቢያስገኝም፤ በተለይ በከተሞች አካባቢ አሁንም ጠንከር ያለ የኑሮ ውድነት ጫና መኖሩ እንደማያጠያይቅ አመላክተዋል፡፡
 
መንግስት ዝቅተኛ ደመወዝ ላላቸው የመንግስት ሠራተኞች 300 ፐርሰንት ደመወዝ ጨማሪ ማድረጉን በማስታወስም፤ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ እና የገቢ ምንጭን ማስፋት ላይ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
 
ለዚህም ከማሻሻያው በኋላ አርሶ እና አርብቶ አደሩ አካባቢ ያለውን የገቢ ጭማሪ ለአብነት አንስተዋል፡፡
 
በኩታገጠም በሚታረሱ አካባቢዎች እንደ ሀገር የአርሶ አደሩ ምርታማነት በ28 እና 29 በመቶ መጨመሩን በማንሳትም የአርሶአደሩ ገቢ በ18 በመቶ እንደጨመረ ተነግሯል፡፡
 
ይህ ቁጥር ቀላል አይደለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በመኸር ወቅት ከሚታረሰው ግማሽ ያህሉ በኩታ ገጠም መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዚህም በሌማት ትሩፋት፣ በማር፣ በወተት፣ በዶሮ እና በሌሎች ሥራዎች እየተገኙ ያሉ ውጤቶችን አመላክተዋል፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top