የሀገራዊ ምክክር ሂደት የብዙ ከዋኞችን ተሳትፎ የሚፈልግ የዲሞክራሲ እና የሰላም ግንባታ ሂደት ነው፡፡ ሂደቱ በርካታ ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ ሆኖ በተለያየ የዕድሜ ወሰን ውስጥ የሚገኙ፣ በተለያየ የሕይወት ተሞክሮ ውስጥ የሚያልፉ፣ እና በማህበረሰባቸው ውስጥ የተለያየ ሚና የሚጫወቱ ዜጎችን ያሳትፋል፡፡
በሀገራችን ኢትዮጵያም እየተካሄደ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ሂደት በተለያዩ የዕድሜ ክልሎች የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የትውልዶችን ተሳትፎ እና መስተጋብር በማበረታታት እና በጋራ ችግሮቻቸው ላይ መነጋገር እንዲጀምሩ በማድረግ አበረታች ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡
ሂደቱ በተለይም በአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ ላይም ወጣቶች እና አረጋውያን ከሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን እንዲወያዩ እና አጀንዳዎቻቸውን እንዲያዘጋጁ መፍቀዱ በትውልዶች መካከል የሚደረግን የምክክር ባህል ለማስጀመር ያደረገው አንድ ወሳኝ እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
ሂደቱ የተለያዩ ትውልዶች በሀገራቸው ጉዳይ ተቀምጠው ለመመካከር መፍቀዳቸው በመካከላቸው ያሉ የሀሳብ ልዩነቶች ወደ መሬት ወርደው ውይይት እንዲደረግባቸው ጋባዥ ሁኔታን ሲፈጥር ተስተውሏል፡፡ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሀሳቦች በተለያዩ ትውልዶች መካከል የሚደረጉ ምክክሮች ሂደት የሚኖረውን ዋና ዋና ጠቀሜታዎች ያስረዳሉ፡፡
1. የጋራ ግንዛቤን በመፍጠር መግባባት ላይ ለመድረስ ማገዙ
አረጋውያን፣ ጎልማሶች እና ወጣቶች በትላንቱ፣ በዛሬው እና በነገው የሀገራችን ጉዳይ ላይ በመነጋገር አንዱ በሌላው ያለውን የተዛባ አመለካከት በማጥራት በትውልዶች መካከል የተፈጠረን ክፍቶችን ለመሙላት ያግዛል፡፡ ይህም የተሻለ መቀራረብን፣ መነጋገርን ብሎም መግባባትን ይፈጥራል፡፡
2. የስሜት ሕመሞችን እና ጠባሳዎችን ለማከም ማገዙ
በሀገራዊ ምክክር ሂደቶች የተለያዩ ትውልዶች በሀገራችን ጉዳዮች ላይ ለመወያየት መፍቀዳቸው በሀገር ጉዳይ የተለያየ መስዋትነትን የከፈሉ፣ ጠባሳ ያለባቸው እንዲሁም ለስነ-ልቦና ሕመም ለተዳረጉ ጎልማሶች እና አረጋውያን ህመማቸውን ለማከም በር ይከፍታል፡፡ ይህም ያለፈው ትውልድ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ያበረከተውን አስተዋፅኦ፣ ጀብድ እንዲሁም ስህተቶችን አንስቶ ለመወያየት በር ስለሚከፍት የአሁኑ ትውልድም ከዚህ ትምህርት በመውሰድ ላለፈው ትውልድ ሰብዓዊ ሀዘኔታን እንዲቸረው በማድረግ የስነ-ልቦና ጉዳትን ለማከም በር ይከፍታል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ሂደት የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎ የሚፈልግ እና የሚያበረታታ የዲሞክራሲ ሂደት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ በሂደቱ በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ዜጎች (ወጣቶች፣ ጉልማሶች እና አረጋውያን) መሳተፋቸው ሂደቱን ምሉዕ ለማድረግ የራሱን ሚና የሚጫወት ከመሆኑም በላይ አካታችነትን ያረጋግጣል፡፡