መንግሥት በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 32 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሕንድ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል በማይናማር በእገታ ሥር ቆይተው ወደ ታይላንድ ከተሻገሩ 133 ኢትዮጵያ መካከል 32ቱ ዛሬ ወደ ሀገራቸው መግባታቸው ተገልጿል።
43 ኢትዮጵያውያን ደግሞ ዛሬ ምሽት ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ በመረጃው ተመላክቷል።
ቀሪዎቹ በታይላንድ ማቆያ የሚገኙ 58 ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ኤምባሲው ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተጠቅሷል።
በተያያዘ መንግሥት ጃፓን በሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ወደ ታይላንድ በማሻገር ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
ሕብረተሰቡ በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሀሰተኛ ቅስቀሳ ተታሎ የሥራ ስምሪት ውል ወደ አልተፈጸመባቸው ሀገራት ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲቆጠብ ሚኒስቴሩ አሳስቧል።