የኢትዮጵያ ጦር “ከባለ ሙዝ ቅርጿ ጨረቃ” የጦር አሰላለፍ እስከ ድል

8 Days Ago 429
የኢትዮጵያ ጦር “ከባለ ሙዝ ቅርጿ ጨረቃ” የጦር አሰላለፍ እስከ ድል

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ጦር አንድ ቦታ ላይ ተዋግቶ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ጦርነቱን ከፍፃሜ ላይ በማድረስ ተመልሶ እንዳይካሄድ ማድረግ ያስቻለ የኢትዮጵያውያን ተጋድሎ ውጤት ነው።

የጣሊያን ጦር ዓድዋ ላይ ተሸንፎ፣ ስንቅ ትጥቁን ጥሎ፣ የሞተው ሞቶ፣ የተማረከው ተማርኮ፣ የተቀረው እግሬ አውጭኝ ብሎ ከመረብ ምላሽ ሲሸሽ በዚያው ወቅት ከጣሊያን ከ15 ሺህ በላይ ወታደሮችን ጭኖ የተነሣ እና ለጦሩ ድጋፍ ለመስጠት ያለመ ጦር በባህር ላይ ለወራት ተጉዞ ከወደብ ደርሶ እንደነበር የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር አየለ በከሬ ይገልጻሉ።

ነገር ግን የዓድዋው ድል የማያዳግም ትምህርት ለጣሊያኖቹ ሰጥቶ ስለነበር ምፅዋ ወደብ የደረሰው ተጨማሪ ከ15 ሺህ በላይ የጣሊያን ጦር ጦርነቱን ለመቀጠል ምንም ዓይነት ሙከራ ሊያደርግ አልቻለም ነበር።

ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ጦር በታላቁ የዓድዋ ድል ጣሊያንን በጦር ሜዳ ላይ ብቻ ማሸነፍ ሳይሆን እብሪተኛው ጣሊያን መልሶ ኢትዮጵያን እንዳይወጋ የተዋጣለት የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ ነድፎ የተንቀሳቀሰ እና ድሉን ያፀናም ነበረ የሚባለው።

የኢትዮጵያ ጦር በውጊያ ወቅት የአዲስ ጨረቃ ቅርፅ ያለው የጦር አሰላለፍ እንደነበረው የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ ይላሉ ፕሮፌሰር አየለ።

ኢትዮጵያውያኑ የዓድዋ ጀግኖች እንደየ መልክዓ ምድሩ አመቺነት በጅምር ጨረቃ ቅርፅ፤ ከግራ እና ከቀኝ እንዲሁም ከመሐል ሆነው ተሰልፈው ገብተው ጠላትን ይገጥማሉ።

በዚህ የጦር አሰላለፍ ከመሐሉ ልክ “እንደጅምሯ ጨረቃ ሆድ” ሰፋ ባለው ስፍራ ላይ አብዛኛው ጦር ተከማችቶ ይገኛል። ከበስተግራ እና ከቀኝ የጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ጦር ቁጥር እንደጨረቃዋ ቅርፅ እየሳሳ እየሳሳ ይመጣል። ታዲያ ይህ የሚሆነው በምክንያት ነው። መሐል ላይ ያለው ጦርነት እየበረታ ሲመጣ ከግራ እና ከቀኝ ያለው ጦር ወደ መሐል በከበባ ከገባ በኋላ ጠላትን ለወሬ ነጋሪ እንኳን ሳያስተርፍ ለመደምሰስ ያመቸዋል።

የኢትዮጵያ ጦር በዓድዋ ጦርነት ጊዜ እስከ 200 ሺህ የሚጠጋ ጦር አሰልፏል፤ በጦርነቱ ደግሞ ትልቁን ሚና የተጫወቱት የፈረሰኛው ጦር እንደነበር ይገለጻል። የጣሊያን ጦር በአንፃሩ አብዛኛው በባንዳ የተደራጀ ከ20 እስከ 30 ሺህ የሚገመት ጦር ሲኖረው በፈረሰኛም ሆነ በእግረኛው የኢትዮጵያዎቹ ጀግኖች ጦር በቁጥር በብዙ እጥፍ ከጠላት ያይል ነበር።

የኢትዮጵያው ጦር “ከባለ ሙዝ ቅርጿ ጨረቃ” የጦር አሰላለፍ ባሻገር በደፈጣ፣ በቆረጣ እና በከበባ የጦር ስልቶች የተካነ እንደነበርም በዓድዋ በተለያዩ ስፍራዎች በተደረጉ ጦርነቶች አስመስክሯል።

ለእውነት፣ በሐቅ፣ ለሉዓላዊነታቸው እና ለነፃነታቸው፤ ያለአንዳች ልዩነት ከዳር እስከ ዳር በነቂስ ወጥተው የንጉሣቸውን የክተት አዋጅ በሙሉ ልብ የተቀበሉት ኢትዮጵያውያን ከፍትሐዊነት ጎን በመቆማቸው ለልባቸው ምሉዕነት እና ለድል ያደረሳቸው ሌላኛው የጦር ሥልታቸው ነበር።

ለአንድ ፍትሐዊ ዓላማ በሙሉ ልብ የቆመ ጦር ሥነ-ልቦና ጣሊያኖቹ ከታጠቋቸው ዘመን አፈራሽ መሣሪያዎች በግልጽ ያይል ነበር።

ለታላቁ የዓድዋ ድል አንዱ ተጠቃሽ ምክንያት የሀገር ፍቅር፣ የዓላማ ፅናት እና የአንድነት መንፈስን የተላበሰ ጦር ማሰባሰብ መቻሉ ነው፤ ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ላይ ለሀገራቸው እና ለነፃነታቸው ያላቸውን የማይናወጥ ፍቅር በግልጽ አሳይተዋልና።

የኢትዮጵያን የዘመናት የጦርነት ልምድ እና የጦር መሪዎቹ ብልሃት የተሞላባቸው ውሳኔዎች፣ እዚህ ጋር “የእነ ባሻ አውአሎም ድንቅ የስለላ ጥበብ ልብ ይሏል” የጣሊያንን እብሪተኛ ወራሪ በዓድዋ ተራሮች መካከል ለማስቀረቱ ሌላኛው ተጠቃሽ ጉዳይ ነው።

ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን የወቅቶች መፈራረቅ፣ እጅግ የተለያየ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና የአየር ሁኔታዎችን በጥልቀት መረዳት እና ይህንንም ጥበብ በአግባቡ በዓድዋ ጥቅም ላይ ማዋላቸው ታሪክ ሲዘክረው የሚኖር ሌላው የድል ምክንያት ነው።

እብሪተኛው ጣሊያን በብልጣብልጥ ማወናበጃ ያሰናዳውን የውጫሌ ስምምነት ኢትዮጵያውያን እንደማይቀበሉት ጠንቅቆ ከተረዳ በኋላ ሀገራችንን ለመውረር መነሣቱን የተረዱት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ለመላው ኢትዮጵያውያን ያስተላለፉት የክተት አዋጅ ያዘለው ጥልቅ እና ስሜት ኮርኳሪ መልዕክት፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያን አዋጁን ሰምቶ እና በሙሉ ልቡ ተቀብሎ ወደ ዓድዋ በመትመም በደም እና በአጥንቱ ለትውልድ የተሻገረ ድል ለማውረስ ችሏል።

በወቅቱ አፄ ምኒልክ ያስተላለፉት የክተትአዋጅ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል፦

የዓድዋ የክተት አዋጅ!!

መስከረም 17/1888 ዓ.ም ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጣሊያን ለወረራ መዘጋጀቱን ተከትሎ ያስተላለፉት የክተት አዋጅ።

“እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም። ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም። አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ በፊት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል። እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር። አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም። አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘንህ እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ። አልምርህም። ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም።”

በናትናኤል ፀጋዬ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top