ዓድዋን በጂጂ ጥበብ

8 Days Ago 446
ዓድዋን በጂጂ ጥበብ

በጥልቅ ግጥሞቿ እና ዜማዎቿ ተውበው በተስረቅራቂ ድምጿ የሚንቆረቆሩት ዘፈኖቿ ፍጹም ኢትዮጵያዊ ቀለም የተላበሱ ናቸው - እጅጋየሁ ሽባባው።

ጂጂ ታሪክን እና ባህልን በበሳል ግጥሞቿ፣ በውብ ዜማዎቿ እና በማራኪ ድምጿ መልሳ ስታመጣ ውስጥን ትፈትሻለች። ያላየናትን ትላንት ወደ ቆምንባት ዛሬ አምጥታ ወደ ነገ ተስፋ ታንደረድረናለች። ቁጭትን ውስጣችን ጭራ መንገብገብ ስንጀምር መልሳ ተስፋን ትሰጠናችል። የአባቶቻችን የነጻነት ተጋድሎ ሜዳ ላይ ወስዳ አብራ ታዋጋናለች፤ መልሳ ደግሞ የቆምንበትን እንዳንረሳ ታሳስበናለች።

‘ዓድዋ’ በሚለው ዘፈኗ ላይ ዳሰሳ ያደረገው ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ እሸቱ ‘የእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ሰርክ ገዝፎ የሚንጥ፣ እሩቅ ግን ቅርብ ውብ ስሜት…. ዓድዋ!!’ በሚል ርዕስ ባቀረበው ጹሐፍ፣ ከያኒ ‘አይለወጥም፣ አይነካም ቅዱስ ታሪክ ነው’ ብለን ከታሰርንበት፣ ሀቅ ብለን ካመለክነው አምልኮ አላቅቆ ሌላ መንገድ፣ ሌላ ስርየት እንደሚያጎናጽፈን ሁሉ የእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ዓድዋም ነገረ-መሰረቱ፣ ሌላ እውነት! ሌላ አድማስ! ገዝፎ የሚንጥ፤ እሩቅ ግን ደግሞ ቅርብ ውብ ስሜት አድርጋ አሳይታናለች” ይለናል።

የእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ዓድዋ፣ ስር እና መንፈሱ ድሮ ጥንት ተጉዞ፤ የሰው ልጅ ‘ሀ’ ብሎ ሲፈጠር ከተሰጠው ጸጋ እና ክብር እንደሚጀመር የሚጠቅሰው ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ፣ “የሰው ልጅ ክቡር፤ ሰው መሆን ክቡር…” የሚለውን ስንኟን እንደ ዋቢ ያቀርባል። ጂጂ ዓድዋን፣ “የሰው ልጅ ክቡር፣ ሰው መሆን ክቡር” ብላ አሐዱ ያለችበት መንገድ ‘ታሪከ-ዓድዋ’ን ያየችበት፣ ሐቁን የተገነዘበችበት እና እንዲተኮር የፈለገችው ትርጓሜ ነውም ይለናል።

የሰው ልጅ ትልቁ ጸጋ፣ ሰው ሆኖ የመፈጠር፣ ተፈጥሮም በክብር የመኖር ጸጋ ሲገፈፍ ሰው መሆኑ ጎዶሎ እንደሚሆን ያሳየችበት እንደሆነና ዓድዋ ላይ የተከፈለው መሥዋዕትነት ይህን ለሰው ልጅ የተሰጠውን ጸጋ ለመጠበቅ እንደሆነ ማሳየቷን ያወሳል። የሰው ልጅ ከተሰጠው ክብር አንሶ፣ ወርዶ እና ረክሶ እንዳይቀር በዓድዋ “ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን…” ብላ የተከፈለውን መሥዋዕትነት ምክንያት ታጎላለች።

ጂጂ፤ ‘ዓድዋ’ በሚለው ሙዚቃዋ የምትነግረን ለሰው መሞት፣ ለሰው ክብር መሠዋት፤ ከምንም በላይ ሰው ክቡር መሆኑን መገንዘብ የዓድዋ አባቶቻችን በአፍ ሳይሆን በተግባር ሳያጎድሉ መከወናቸውን ነው።

በሙዚቃው ወስጥ ጀግኖች አባቶቻቻን የሰው ልጅ ክቡር፣ ሰው መሆን ክቡር መሆኑን ተገንዝበው እና አስገንዝበው እንዳለፉ አጽንዖት ሰጥታው ማለፏን ያስታውሰናል ረዳት ፕሮፌሰሩ።

ለሰው ክብር ሲባል መሞት ትልቁ የፍቅር መገለጫም በኛው ሀገር፣ በዓድዋ ተራራ ሲከወን ያሳየችው “በክብር ይሄዳል፣ ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ…” እያለች እንደሆነ ስንኞቿን መዝዞ ያሳየናል።

“ሰው ተከፍሎበታል ከደም እና ከአጥንት…” ስትለንም አባቶቻችን የሕይወት፣ የመዳን፣ የፈውስ፣ የቤዛ ምልክቶች ብላ ዓድዋን ክብደት ልትሰጠው እንደሆነ ያወሳል። አባቶቻቸን “የሰው ልጅ ክቡር፤ ሰው መሆን ክቡር…” ብለው ስለከወኑት፤ ደግሞም ውድ ሕይወታቸውን ሳይሰስቱ፣ በደግነት፣ በፍቅር፣ ሰጥተው ስላለፉ፤ ለዛሬ ሳይጓደል ለተገኘ ነጻነት ሕያው ምሥክር እንደሆኑ ምስክር ስትጠቅስም “ትናገር ዓድዋ፣ ትናገር ትመስክር፤ ትናገር ዓድዋ፣ ትናገር ሀገሬ…” እያለች ቋሚ እማኝ፤ ቋሚ የታሪክ ምሥክር ትጠራለች። ሕያው አብነትነቱም በእኛ በልጆቻቸው ልቦና ውስጥ ሕይወት ዘርቶ፤ ግዘፍ ነስቶ በዘላቂነት እንዲኖር ማድረጓን ይጠቅሳል።

“ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን…” ስትለን አባቶቻችን ለሰው ላላቸው ክብር እና ፍቅር ሲሉ ትውልድ እንዲኖር እነርሱ መሞታቸውን እየጠቀሰች ቀጥላ፣ “ሰው ተከፍሎበታል ከደም እና ከአጥንት…” ብላ ታጠናክረዋለች። በዚህም በእጅጋየሁ ሽባባው ዓድዋ ሰው በክብር ለሰው መድኅን እንዲሆን እንጂ "… ወራሪን ለመመከት፣ ሀገር ለመሥራት፣ ቅኝ ግዛትን ለማውገዝ ወዘተ ለሚባሉ" ሰርክ ለምንሰማቸው ምክንያቶች እንዳለሆነ ያወሳል።

“የሰው ልጅ ክቡር፤ ሰው መሆን ክቡር…” ብላ ጀምራ፣ አባቶቻችን የወደቁት ወራሪን ገጥሞ ለመጣል ነው ብትል የተነሳችበትን የዳጎሰ እና ፍጹም የሆነ የሀሳብ ልዕልና የታየበትን አድማስ ያኮስስባት እንደነበረ የሚገልጸው ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ፣ እሷም የተነሳችበት ሀሳብ ይበልጥ ይጎለብት ዘንድ፤ የሰው ልጅ ሰውን በመውደድ፣ ሰው መሆን ክቡር መሆኑን በተግባር ሲገልጥ ሌላ የደረጀ ሀሳብ ባለቤት ይሆናል፤ እሱም የደረጃ ነጻነትን ይጎናጸፋል ትለናለች” በማለት ነው የሀሳቧን ግዝፈት የሚያወሳው።

ነጻነትም ሰው ሆኖ ከመፈጠር ጋር የሚሰጥ እንጂ የማንም ችሮታን እንደማይጠይቅ፣ ጥንት አባቶቻቻን እንደተረዱት በጂጂ ሙዚቃ ውስጥ በጉልህ ተመልክቷል። በሙዚቃው፣ የጻነት ትርጓሜ ደግሞ ምንጩ የሰው ልጅ ክቡር እንደሆነ መረዳትና ለዚህም ራስን አሳልፎ መስጠት እንደሚያስፈልግ አስገንዝባለች፤ - እጅጋየሁ ሽባባው።

እንደካባ የተጎናጸፈችውን ነጻነት፣ “በኩራት፣ በክብር፣ በደስታ፣ በፍቅር፤ በድል እኖራለሁ ይኸው በቀን በቀን…” እያለች ታሽሞነሙናለች።

የእጅጋየሁ ሽባባው ዓድዋ የትላንት በፊትን፣ ከትላንት ጋር ብቻ አስተሳስሮ ለማለፍ አልተጋም። ይልቅስ ዓድዋ ትላንትን ከዛሬ ጋር ሲያዛምድ፣ ሲሰፋ ይታያል። “ዓድዋ ዛሬ ናት፣ ዓድዋ ትናንት….” እያለ፤ ከትናንት ሽቅብ ወደ ዛሬ ይንደረደራል። “ሰው መሆን ክቡር” ያሉ የጀግኖች አባቶቻችን ርዕይ ሜዳ ላይ ብቻ፣ በወሬ ብቻ ወድቆ መቅረቱ ጂጂን ያንገበገባት እንደሚመስለው በቅኝቱ ያሳየናል። እንደሱ አባባል በጂጂ ዓድዋ ጀግኖች አባቶቻቻን በክብር አላረፉም። የሚያሳርፉ ልጆች አላገኙምና ቁጭቷን “ዓድዋ ዛሬ ናት ዓድዋ ትላንት፤ መቼ ተነሡና የወዳደቁት…” የምትለን ለዚህ ነው ይለናል። የዛሬው ትውልድ በተራ ነገሮች ሲናቆር ያን አባቶቻችን የወደቁለትን ታላቅ ዓላማ ከግብ አለማድረሳችን ያንገበግባታል።

ትላንት “በነጻ ምድር” ስለሰው ልጅ ክብር ሲባል ደም እና አጥንቱን ከፍሎ ሀገሩን፣ ኢትዮጵያን የአፍሪካ እና የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ቀንዲል እንድትሆን ያደረገ ጀግና በተፈጠረበት ሀገር፣ ዛሬ ኢትዮጵያ የሀገር-ተከታይ፤ የድህነት ምሳሌ፣ ጭቁን፣ የጉስቁልና ምድር ስትሆን የወደቁት አባቶቻችን አጥንት ገና በክብር አልተሰበሰበም። ሕያው ሀገር፣ ነጻ ሀገር ለመፍጠር የወደቁ አባቶች በነበሩበት ሀገር ወደ ጎጥ ወርዶ ሽኩቻ ውስጥ መግባት የእነዚያን አባቶች መሥዋዕትነት ከንቱ ማድረግ ነው።

“ትላንት ሰው የሚባል አርማ አንስተው፣ ሰው በሚባል የወል ስም ለሰው የሞቱ አባቶች በነገሡበት ሀገር፣ ዛሬ ‘ዓድዋ ላይ የተታኮሰው ቀኝ አዝማች እከሌ፣ የወደቀው ደጃዝማች እከሌ እኮ ብሔሩ እንትን ነው... የኛ ጀግና ሳይሆን የኔ ዘር ብቻ ጀግና ነው…’ በሚባልበት ሀገር፣ የሞቱትን አላሳረፈምና፤ ተከታይም አላፈሩምና ጂጂ ‘ዓድዋ ዛሬ ናት፣ ዓድዋ ትላንት፤ መቼ ተነሡና የወዳደቁት…’ ብትል፤ አብዝታም ብትቆጭ የሚጨበጥ አመክንዮ አላት” ይላል ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ እሸቱ።
ሌላው ጂጂ፣ “ዓድዋ ዛሬ ናት፣ ዓድዋ ትላንት” ስትል ያዛመደችው እውነተኛ ከሆኑት የዛሬ የዓድዋ ልጆ ጋር ነው። ሰውን በሰውነቱ ለሚወዱ፣ ሀገራቸው ነጻ ሀገር እንደሆነች ለሚያሰቡ፣ “እኔ ኢትዮጵያ ነኝ” ለሚሉ፤ የሰው ህመም ህመማቸው፣ ስቃዩ ስቃያቸው ለሆነባቸው፤ ሀገራቸው የምንግዜም ጌጣቸው የሆነችላቸው የዛሬ የዓድዋ እውነተኛ ልጆችን እጅጋየሁ ሽባባው በተቃራኒው እንዲህ ትላቸዋለች፤ “በኩራት፣ በክብር፣ በደስታ፣ በፍቅር፤ በድል እኖራለሁ ይኸው በቀን በቀን!…”

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top