ልክ የዛሬ 129 ዓመት በዓድዋ ተራሮች ዓለም በተለይም አውሮፓውያን ያልጠበቁት ክስተት ተፈጠረ። አውሮፓውያን እንደቅርጫ የተከፋፈሉት ጥቁር ሕዝብ ድል አደረጋቸው።
ኢትዮጵያውያን ቀድመው የጀመሩትን የፀረ-ባርነት ትግል የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ረፋድ ላይ አጠናቅቀው የጥቁር ሕዝብን የድል ችቦን ለኮሱ።
ይህ ወሳኝ ድል ሀገራችንን ቀጣይነት ያለው ነፃነት ያረጋገጠ ሲሆን ኢትዮጵያ የአውሮፓ ቅኝ አገዛዝን በተሳካ ሁኔታ መቋቋም የቻለች ብቸኛዋ የአፍሪካ ሀገር እንድትሆን አድርጓታል።
ይህ ስኬት የተመዘገበው ደግሞ በላቀ የጦር ስትራቴጂ፣ በኢትዮጵያ ኃይሎች መካከል በነበረው አንድነት እና ኢትዮጵያውያን ስለ ነፃነት አስፈላጊነት በነበራቸው ግንዛቤ ምክንያት እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።
ለመሆኑ የዓድዋ ድልን ውጤታማ ያደረጉት የጦርነት ሥልቶች ምን ምን ናቸው?
- ብቁ አመራር እና አንድነት
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን አንድ በማድረግ ከእቴጌ ጣይቱ፣ ራስ መኮንን፣ ራስ መንገሻ፣ ራስ አሉላ ጨምሮ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከተውጣጡ የጦር አመራሮች ጋር በመናበብ እና ብቁ አመራር በመስጠት የድሉን ጎዳና ጠርገዋል።

በተለይም በግዛት ማስፋፋት ምክንያት በጦርነት ውስጥ የነበሩ የኢትዮጵያ ክፍሎችን ያስተባበሩበት ጥበብ የአመራር ብቃታቸው ማሳያ ነው። ኢትዮጵያውያኑም የውስጥ ቅራኔያቸውን ወደ ጎን በመተው የሀገርን ነፃነት ያስቀደሙበት የሀገር ፍቅር እጅግ የሚደነቅ ነው።
ንጉሡ እና የጦር መሪዎቻቸው የተጠቀሙት የዲፕሎማሲ ጥበብም ሌላው ለድሉ መገኘት የራሱን ሚና የጠጫወተ ጉዳይ ነው። ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በብልሃት እና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ በመለየት ከፈረንሳይ፣ ከሩሲያ እና ከብሪታንያ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን በማግኘት እግረ መንገዳቸውንም ጣሊያንን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመነጠል ያደረጉት ጥረት ለጦርነቱ ውጤት የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል። ከጣሊያን ጋርም ቢሆን የፈለጉትን ነገር እስከሚያገኙ እና የውጫሌ ውል 17ኛው አንቀጽ ሴራ እስከሚጋለጥ ድረስ የተለሳለሰ አቋም ይዘው ቆይተዋል።
ተዋጊ ኃይል የማሰባሰብ ጥበባቸውም ሌላው ለድሉ መገኘት ምክንያት የሆነ ጉዳይ ነው። ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የጦርነቱን የክተት አዋጅ በማወጅ ፈረሰኞችን፣ እግረኞችን፣ የመድፍ አደላዳዮችን ጨምሮ ከ100 እስከ 120 ሺህ የሚጠጉ ተዋጊዎችን ማሰባሰብ ችለዋል።
ለዚህም የተጠቀሙበት ሥልት በክተት አዋጁ ላይ እንደሚታየው የተለሳለሰ እና ልመና መሰል መልዕክትም፣ ጠንከር ያለ ትዕዛዝንም በመቀላቀል ነው።
“ሀገር የሚያፈርስ፣ ሃይማኖት የሚቀይር ጠላት” ባሕር ተሻግሮ ድንበር አቋርጦ መምጣቱን በመጥቀስ፣ ሁሉም አቅሙ የሚችለው ሁሉ አብሯቸው እንዲዘምት፣ አቅም የሌለው በጸሎቱ እንዲያግዛቸው፣ ይህን ሳያደርግ ለቀረ ግን ምሕረት እንደሌላቸው በማርያም ምለው ነው ያሳሰቡት።
ይህ ሥልት ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚችለው መልክ የዓድዋ ዘመቻ ተባባሪ እንዲሆን አድርጎታል።
ሕዝቡም አንድም ሀገሩ በባዕድ መወረሯ በፈጠረበት ቁጭት፣ በሌላ በኩል ለመሪው ባለው ታማኝነት በአንድ አዋጅ ተጨማሪ ቅስቀሳ ሳይፈልግ ስንቁን እና ትጥቁን ይዞ ወደ ዓድዋ በመትመም አንጸባራቂውን ድል አስመዝግቧል።
- ሥልታዊ የመልክዓ ምድር አጠቃቀም
የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ለጠላት ፈተና ለኢትዮጵያውያን ደግሞ መከታ ነው። በዚህ ምክንያት መልክዓ ምድራቸውን በትክክል የሚያውቁት የኢትዮጵያ ኃይሎች ተራሮቹን፣ ሸለቆዎቹን እና ሜዳዎቹን እንደ አጋር ተጠቅመውባቸዋል።

በተለይም የካቲት 23 ቀን የተደረገው የማጠቃለያው ጦርነት የተደረገበት የዓድዋ ተራራ ጣሊያኖችን ግራ በማጋባት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስከበር ውስጥ ሚናቸውን ተወጥተዋል። እናም እንኳን የኢትዮጵያ ሰው የኢትዮጵያ መሬትም ለባዕዳን ወራሪ እንደማይመች የዓድዋ ተራሮች ምስክሮች ሆነው አልፈዋል።
ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ቀድመው የተራሮቹን ከፍተኛ ቦታዎች መያዛቸውም የጣሊያንን እንቅስቃሴ በትክክል ለማየት እና ቀድመው ለማጥቃትም የዓድዋ ተራሮች ጠቅመዋቸዋል።
በዓድዋ ጦርነት የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን በሰላም ጊዜ አራሾች፣ በጦርነት ጊዜ ተኳሾች ናቸው። ይህ ባህሪያቸው ደግሞ የአየር ጠባይም ሆነ ጭለማ ሳይበግራቸው ባሻቸው ጊዜ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል።
የካቲት 22 ለየካቲት 23 አጥቢያ ሌሊት የተከሰተውም ይኸው ነበር። ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ይህን በሌሊት የመጓዝ ብቃታቸውን ተጠቅመው ነው ወራሪውን የጣሊያን ኃይል ባልጠበቀበት ሰዓት ከሌሊቱ 11 ሰዓት ጀምረው የቀደሙት።
- መረጃን የመሰብሰብ እና በትክክል የመጠቀም ብቃት
እነ ራስ አሉላ እና ራስ መኮንን በሠሩአቸው የመረጃ ሥራዎች የጣሊያንን ኃይል በከፍተኛ ሁኔታ አዛብተዋል። በተለይም ራስ መኮንን ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጋር እንደተቀያየሙ መወራቱ ጣሊያን አፄ ምኒልክ ቀኝ እጃቸውን አጥተዋል ብልው እንዲያምኑ እንዳደረጋቸው ይወሳል።

ራስ አሉላ በበኩላቸው፣ በትግራይ አካባቢ የሚያውቁአቸውን ሰዎች ወደ ጣሊያን ሠፈር አስርገው በማስገባት የጠላትን አሰላለፍ እና አቅም ቀድመው መረዳት ችለዋል።
እነዚህ የከዱ መስለው ወደ ጣሊያኖች የተላኩት ኢትዮጵያውያን የጣሊያንን የጦር ሠራዊት እንቅስቃሴን የተመለከተ ትክክለኛ መረጃን ለንጉሡ ሲሰጡ፣ በአንጻሩ ደግሞ ለጣሊያኖች የተሳሳተ መረጃ በማቀበል የኢትዮጵያን ጥንካሬ በተሳሳተ መንገድ እንዲያሰሉ አድርጓቸዋል።
እነ ባሻይ ኣውዓሎም ደግሞ በዚህ ረገድ እጅግ ከፍተኛ ጀብዱ የፈጸሙ የኢትዮጵያ ባለውለታዎች ነበሩ። ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ የጠላትን ትኩረት የማዛባት ሥራ ከሠራች በኋላ የወሰደችው ፈጣን ማጥቃት ጣሊያኖችን ግራ አጋብቶ ለመራራ ሽንፈት ዳርጓቸዋል።
- ውጤታማ ወታደራዊ አመራር እና ድንቅ ጀግንነት
ንጉሡን ጨምሮ በየደረጃው ያሉት የጦር አመራሮች የከበባ ሥልትን በመጠቀም ጠላትን የመቁረጥ ሂደትን በመከተል ነው ጣሊያን ላይ ጥቃት የፈጸሙት። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ኃይሎች የጣሊያንን ጦር ከበቡት።

ወደኋላ የሚሸሹበትን መንገዳቸውን በመቁረጥ እና መረጃ ከአንዱ የጣሊያን ጦር ክፍል ወደ ሌላው እንዳይደርስ በማድረግ ግራ እንዲጋቡ አደረጓቸው።
በተለይም ከዋናው ማዘዣ ጣቢያ እና ከጄኔራሎቹ ጋር ያለው ግንኙነት ባላሰበበት ወቅት የተቆረጠበት የጣሊያን ጦር ግራ በመጋባት ትርምስ ውስጥ ገባ። ኢትዮጵያውያን ጀግኖችም አመራሮቹን ቀድመው በመምታት ጦሩን አመራር አልባ በማድረግ የወደቀው ወድቆ ሌላው ሲማረክ የቀረው እግሬ አውጪኝ ሽሽት ውስጥ ገባ።
የጣሊያን ጦር ግራ ተጋብቶ ያለውን ጥሎ ሲሸሽ ኢትዮጵያውያኑ ጀግኖች ከራሱ ከጣሊያን ያገኙትን ዘመናዊ ጠመንጃ እና መድፍ በመጠቀም ድሉን አፋጠኑት።
የኢትዮጵያ ሠራዊት ፈጣን ፈረሰኞችን እና እግረኞችን በመጠቀም ፋታ የሚነሣ ጥቃት በማድረስ የጣሊያንን ጦር ከረፋዱ አምስት ሰዓት ላይ በታተነው።
በአጣቀላይ ኢትዮጵያ በስትራቴጂክ የጦር ዕቅድ፣ በአንድነት እና በሥልታዊ ብልጠት የጣሊያንን የቅኝ ግዛት ጥረት በተሳካ ሁኔታ ያመከነችበት ድል ነው - ዓድዋ።
በለሚ ታደሰ