ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ብሔራዊ ጥቅሟን መጠየቅ ትቀጥላለች፡- አምባሳደር ነብያት ጌታቸው

28 Days Ago 337
ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ብሔራዊ ጥቅሟን መጠየቅ ትቀጥላለች፡- አምባሳደር ነብያት ጌታቸው
ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ብሔራዊ ጥቅሟን መጠየቅ ትቀጥላለች ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ተናገሩ።
 
በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስምምነቶች መደረጋቸውን አምባሳደር ነብያት ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
 
ቃል አቀባዩ በቱርክ አንካራ የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ነበረበት መመለስ ተችሏል ብለዋል።
 
በሀገራቱ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት በየደረጃው ውይይት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሶማሊያ ሞቃዲሾ በነበራቸው ቆይታ ሁለቱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት መደረጉን ገልፀዋል።
 
የሀገራቱ ስምምነት የሁለትዮሽ ግንኙነትን ከማጠናከር በዘለለ ለቀጠናው ሰላም ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ያሉ ሲሆን፣ የአልሸባብን የሽብር ቡድን በጋራ ለመከላከልም ስምምነት ላይ መደረሱ ተጠቅሷል።
 
ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ግንኙነት ወደ ነበረበት መመለሱ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል መሆኑን የገለጹት ቃል አቀባዩ፤ ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን የባሕር በር የማግኘት መብቷን ትጠይቃለች ብለዋል።
 
በመስከረም ቸርነት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top