የዓድዋ ድል ሚስጥር የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ መቆሙ ነው፦ የታሪክ መምህር

29 Days Ago 327
የዓድዋ ድል ሚስጥር የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ መቆሙ ነው፦ የታሪክ መምህር
ከዛሬ 129 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የተፈፀመው የዓድዋ ድል የሀገርን ዳር ድንበር ለወራሪ ጠላት አሳልፎ ላለመስጠት የተደረገ አስደናቂ ድል ነው፡፡
 
ለሀገር ሉዓላዊነት በኅብረት በመቆም የሕይወት መስዋዕትነት የተከፈለበት የዓድዋ ድል፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው፡፡
 
በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የታሪክ፣ የፌደራሊዝም እና የአካባቢ አስተዳደር ጥናት መምህር የሆኑት አቶ ዓይነኩሉ ጎሀፅባህ፤ የዓድዋን ድል በተመለከተ በዛሬው የኢቲቪ አዲስ ቀን "የሀገር ጉዳይ" መሰናዶ ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
 
የታሪክ መምህሩ ለዓድዋ ድል መገኘት ዋናው ሚስጥር የኢትዮጵያ ህዝብ በጋራ መቆሙ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
 
 
ይህ ድል የነጮቹን የመግዛት እና የመጨቆን ስሜት ያበረደ ስለመሆኑ ገልጸው፤ ቅኝ ገዢዎችን አንገት ያስደፋ አፍሪካውያንን ደግሞ ቀና ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
 
ድሉ በቀላሉ የተገኘ አይደለም የሚሉት መምህሩ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሕይወት መስዋዕትን የከፈለበት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
 
የሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የነፃነት እንቅስቃሴ ታሪክ ጅማሮ የዓድዋ ድል መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዓድዋ ድል አንድነት እና ኅብረትን ልንማር ይገባል ብለዋል፡፡
 
ልንደራደር ከማንችልባቸው ነገሮች መካከል የሀገር ጉዳይ ዋነኛው ነው የሚሉት የታሪክ መምህሩ፤ ጀግንነት በጦር ሜዳ ብቻ ባለመሆኑ ትውልዱ ለሀገሩ በየትኛውም መስክ ድል ማስመዝገብ አለበት ሲሉ መክረዋል፡፡
 
የአሁኑ ትውልድ የተሻለች ሀገር በመገንባት የዓድዋን ድል ሊደግም ይገባልም ብለዋል፡፡
 
ዓድዋ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቁ ድል ነው የሚሉት ደግሞ የታሪክ መምህሩ አቶ በላይ ስጦታው ናቸው።
 
የዓድዋ ድል በቂ ቴክኖሎጂ እና ዘመናዊ ትራንስፖርት ባልነበረበት ወቅት መሆኑ ድሉን አስደናቂ ያደርገዋል ሲሉ ነው የገለጹት፡፡ ይህ ድል ዓለም አቀፍ የሆነ አንጸባራቂ ድል ነው ብለዋል፡፡
 
ዓድዋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲደርስ የነበረው ጭቆና እንዲቆም ምክንያት ሆኗል ያሉ ሲሆን ዓለም አቀፍ እሳቤን የቀየረ ስለመሆኑም አያይዘዋል፡፡
 
የሰውን ልጅ አስተሳሰብ እና ፍልስፍናን የቀየረ መሆኑን አንስተው፤ የሰው ልጅ እኩል ነው፤ የሰው ልጅ ክቡር ነው፤ ለሚለው እሳቤ መነሻው ሆኗል ብለዋል፡፡
 
በሜሮን ንብረት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top