የሚዘጋጀው የኢትዮጵያ የማንነቶች መገለጫ ለሀገር በብዙ መልኩ ጥቅም ይኖረዋል፡- የፌደሬሽን ምክርቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

30 Days Ago 332
የሚዘጋጀው የኢትዮጵያ የማንነቶች መገለጫ ለሀገር በብዙ መልኩ ጥቅም ይኖረዋል፡- የፌደሬሽን ምክርቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የማንነት መገለጫ ለማዘጋጀት የስምምነት ፊርማ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
 
የፌደሬሽን ምክርቤት ከኢፌዴሪ ባሕልና ስፓርት ሚኒስቴር እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የማንነት መገለጫ አትላስን (የኢትኖግራፊና የቋንቋ ባህርያት) ፕሮፋይል ለማዘጋጀት የሦስትዮሽ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል።
 
ስምምነቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) ፈርመውታል።
 
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የአትላሱን መዘጋጀት ጥቅም ያብራሩት አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ የሚዘጋጀው የኢትዮጵያ የማንነቶች መግለጫ ለሀገር በብዙ መልኩ ጥቅም ይኖረዋል ብለዋል።
 
አፈ ጉባኤው በምክርቤቱ የተመዘገቡት ብሔረሰቦች 76 መሆናቸውን ገልፀው፤ ከቁጥሩ ጀምሮ በእርግጠኝነት መናገር የማይቻልባቸው ተያያዥ ጥያቄዎች ሲንከባለሉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
 
በስምምነቱ መሰረትም በኢትዮጵያ ያሉ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እያንዳንዳቸው የት አካባቢ እንደሚገኙ፣ ቋንቋቸው ምን እንደሆነ፣ ባህላቸው ምን እንደሚመስል እንዲሁም መስተጋብራቸው እንዴት እንደሚገለፅ ዝርዝር መረጃዎች ይቀመጥላቸዋል።
 
በዚህም አትላሱ ሲጠናቀቅ ለማንነት ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ብሎም ለጥናትና ምርምር ስራዎች ሁነኛ ማጣቀሻ ሆኖ እንደሚያገለግል ነው የተገለፀው።
 
በሀብታሙ ተክለስላሴ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top