አዲስ አበባን ጨምሮ ትላልቅ ከተሞች ካሉባቸው በርካታ ችግሮች መካከል የመኖሪያ ቤት እጦት በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
በከተሞች የሚስተዋለው የቤት እጦት ጎጆ ቀልሶ ለመኖር ከማይቻልበት ደረጃ ላይ እያደረሰን ነው የሚሉ ድምፆች ከነዋሪዎች ይሰማሉ።
መንግስት እየተገበራቸው ያሉ የቤት ማግኛ አማራጮችም ለችግሩ ሁነኛ መፍትሔ ሊሆኑ አልቻሉም።
አሁን ላይ ደግሞ እስካሁን ከተሞከሩት የቤት አማራጮች ለየት ያለ አማራጭ ለመተግበር እየተሰራ ነው።
በትላልቅ ከተሞች ለሚነሳው የቤት ችግር ሁነኛ መፍትሔ ለመስጠት የቤቶች ፋይናንስ ኮርፖሬሽን እና የቤቶች ፈንድ ለማቋቋም የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ ነው።
የኢትዮጵያ ቤቶች ፋይናንስ ኮርፖሬሽን የቤቶችን ፈንድ የሚያስተዳድር ተቋም ይሆናል።
የቤቶች ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ባንክ እንደሚሆንም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተገልጿል።

ረቂቅ አዋጁ ፀድቆ ወደ ተግባር ሲገባ ከሰራተኞች እና ከአሰሪዎች ከእንዳንዳቸው 1.5 በመቶ በቁጠባ በመሰብሰብ ለቤት ገንቢዎች ብድር እንደሚያቀርብ በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የቤቶች ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ፀጋዬ ሙሼ ተናግረዋል።
የፌደራልና የክልል መንግስታትም ከዓመታዊ የካፒታል በጀታቸው 5 በመቶ ለቤቶች ፋይናስ ኮርፖሬሽን ገቢ እንዲያደርጉ በረቂቅ አዋጁ እንዲካተት ተደርጓል።
ለኢቲቪ አዲስ ቀን "የሀገር ጉዳይ" መሰናዶ ሀሳባቸውን ያጋሩት አቶ ፀጋዬ ሙሼ በከተሞች የመኖሪያቤት ፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣም የቤት ችግሩን አባብሶታል ብለዋል።
የህዝብ ቁጥር መጨመር ደግሞ የቤት ፍላጎትና አቅርቦት እንዳይጣጣሙ ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል።
በዋናነት ቤት ሲገነባ ችግር የሆነው መሬት እና ፈይናንስ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ በማህበር ለሚደራጁ መሬት አቀርባለው ብሏል።
አዲስ የሚቋቋሙት የቤቶች ፋይናንስ ኮርፖሬሽን እና የቤቶችን ፈንድ ደግሞ የፋይናንስ እጥረትን በመፍታት ዜጎች ቤት እንዲገነቡ እድል ይሰጣሉ።
ከዚህ ቀደም መሬት በጨረታ ብቻ ይገኝ እንደነበር አንስተው ከአሁን በኋላ ግን ከጨረታ በተጨማሪ ከመንግስት ጋር በድርድር ስልት መሬት እንዲቀርብ እንደሚደረግ ነው የጠቆሙት።

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መኮንን ሚጀና በበኩላቸው፥ የቤት ችግርን ለማቃለል መንግስት የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎች አሰየወሰደ ይገኛል ብለዋል።
የመንግስትም ሆነ የግል ሰራተኛ ከሚያገኘው ገቢ በመቶኛ በመቆጠብ የቤት ባለቤት የሚሆንበት አማራጭ እየተዘጋጀ ስለመሆኑም አንስተዋል።
ከመንግስት ጋር በመተባበር ቤት የሚገነቡ አጋር ድርጅቶች ጋርም የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙንም ጠቅሰዋል።
በርከት ያሉ አልሚዎች ወደ ስራው ከመጡ የቤት ችግር አቅርቦት እጥረትን ይቀርፋሉ ብለዋል።
የነበሩ የህግ ማእቀፎች እንደ ችግር እንደነበሩ ጠቅሰው አሁን ላይ ማዕቀፉ በመሻሻሉ እንቅስቃሴ መጀመሩን ነው የገለጹት።
በሜሮን ንብረት