በአማራ ክልል ባሕር ዳር ከተማ "ግብር ለሀገር ክብር" በሚል መሪ ሀሳብ የታክስ ንቅናቄና የእውቅና መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ፤ ግብር የአንድን ሀገር ልማት ለማሳለጥና የዜጎችን የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ለመፍታት ቁልፍ መሆኑን ገልፀዋል።
እንደ ሀገር አኮኖሚው የሚያመነጨውን ያክል ገቢን ለማሰባሰብ የታክስ አሰባሰቡ ላይ በተደረጉ የተለያዩ ማሻሻያዎች ለውጦች ቢስተዋሉም በቂ አለመሆኑን ገልፀዋል።
በርካታ የመልማት አቅምና ፀጋዎች ባለቤት የሆነው የአማራ ክልልም የሚሰበስበው ገቢ እየተሻሻለ ቢመጣም የሚፈለገውን ያክል አልደረሰም ብለዋል ሚኒስትሯ።
በመሆኑም በገቢ አሰባሰቡ ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን በመቅረፍና አሰራርን በማዘመን በቅንጅት መስራት ይገባል ነው ያሉት።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው፤ ሁነኛ የፋይናንስ ወጪ የሚሆን ገቢን ለመሰብሰብ ሁላችንም በቅንጅት ልንሰራ ይገባል ብለዋል።
ግብር የተረጋጋ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለመፍጠር ያለውን ፋይዳ ያብራሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ግብርን በአግባቡ ማስተዳደር ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ክልሉ ገቢን ከመሰብሰብ አንፃር ካባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር መሻሻሎች ቢኖሩትም ገና የሚቀሩ ስራዎች አሉ ብለዋል።
የግብር አስተዳደር ሥርዓቱን ማዘመን፣ የግብር አከፋፈል ሥርዓቱን ለግብር ከፋዮች ምቹ የማድረግ እና ሌሎችንም አዳዲስ አሰራሮች በመዘርጋት በጋራ መስራት እንደሚገባም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት።
በክልሉ በበጀት ዓመቱ 7 ወራት 31 ቢልዮን ብር መሰብሰቡም ተመላክቷል።
የንቅናቄ እና እውቅና መድረኩ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ከገቢዎች ሚኒስቴር ባሕርዳር ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት ጋር በጋራ የተዘጋጀ ነው።