“በጾሙ ወራት ስለሀገር ሰላም በመጸለይ እና በመረዳዳት መትጋት ይገባል” ሲሉ የኃይማኖት አባቶች ተናግረዋል፡፡
በዛሬው ዕለት የተጀመረው የዐቢይ ጾም እና መጪው የረመዳን ጾም አማኞች እራሳቸውን ለፈጣሪ የሚያስገዙበት፣ ካላቸው ላይ የሚያካፍሉበት እንዲሁም ለሀገራቸው የሚፀልዩበት ሊሆን እንደሚገባም በኢቲቪ አዲስ ቀን የሀገር ጉዳይ መሰናዶ ተዳሷል፡፡
መጋቢ ሐዲስ ባሕረ ጥበብ አዱኛ ፤ ዐቢይ ማለት ታላቅ ማለት መሆኑን በመግለጽ የእምነቱ ተከታዮች በጾሙ ይበልጥ ወደ ፈጣሪ በመቅረብ እንዲሁም በምስጋና በመትጋት የመላዕክትን ባህሪ እንደሚላበሱ ጠቁመዋል፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስን አርዓያ በመከተል በሚጾመው በዚህ ፆም ስጋ ለነብስ እንደሚገዛም አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል ከቀናት በኋላ የሚጀምረው የረመዳን ፆም የእስልምና ኃይማኖት መመሪያ የሆነው ቅዱስ ቁርዓን የወረደበት ወር በመሆኑ የወራት ሁሉ አለቃ መሆኑን ሼህ እንድሪስ ዓሊ ገልጸዋል፡፡
ቀኑ አማኞች ከሌላ ጊዜ በበለጠ የሚጠያየቁበት፣ የሚተጋገዙበት እና ለመልካም ሥራ የሚተጉበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በጾሙ ወቅት የሚካሄደው የቁርዓን ውድድርም የዘንድሮውን ረመዳን ከቀደሙት ጊዜያት ለየት እንደሚያደርገው አመላክተዋል፡፡
ታዲያ የሁለቱም እምነት ተከታዮች በዐቢይ እና በረመዳን የጾም ጊዜያት በመንፈሳዊ ሥራ የሚበረቱበት ብቻ ሳይሆን በመከባበር ላይ የተመሰረተ መስተጋብራቸውም የሚጠናከርበት ነው፡፡
ረጅም ግዜ በጉርብትና የቆዩት መምህር ሙሉጌታ ለገሰ እና አቶ ጀማል ዑመር ለዚህ ማሳያ ናቸው ፡፡
የተለያየ እምነት ተከታይ የሆኑት ጎረቤታሞቹ በመልካም ወዳጅነት ዓመታትን አብረው ኑረዋል፡፡
ጎረቤታሞቹ በእነዚህ የጾም ወራት ኢትዮጵያውያን ለሀገራችው ሰላም፣ አብሮነት እና ብልፅግና በአንድነት ሊጸልዩ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
አፎሚያ ክበበው