የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስተዳደሩ በበጎነት የመኖሪያ መንደር ለአቅመ ደካሞች እና የልማት ተነሺዎች ያስገነባቸውን 192 የመኖሪያ ቤቶችን የያዙ ሁለት ባለ 9 ወለል ህንጻዎች ለነዋሪዎች በዛሬው ዕለት ለነዋሪዎች አስተላልፈዋል።
ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩ መልዕክት፤ በሰው ተኮር ስራዎቻችን ማህበራዊ ፍትህን ለማንገስ እየሰራን ባለነው ስራ በበጎነት የመኖሪያ መንደር ለመኖር ምቹ የሆኑ ሰባት ህንጻዎችን ገንብተን ለኑሮ ምቹ ካልሆኑ አካባቢዎች ለተነሱ የከተማችን ነዋሪዎች አስተላልፈናል ብለዋል።
በበጎነት የመኖሪያ መንደር የመኖሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን የህጻናት መጫወቻ፣ የእንጀራ መጋገሪያ ፋብሪካ፣ የጸጉር እና የልብስ ስፌት የስራ እድሎች የተካተቱበት ፣ የዜግነት ክብርን የሚመጥን ፣ንፁህ እና ውብ አካባቢ መሆኑንም ከንቲባዋ ገልጸዋል።
አክለውም ከተማችን እንደ ስሟ ውብ፣ አበባ እየሆነች ያለችው የነዋሪዎቿን ኑሮና አኗኗር በማሻሻል ጭምር ነው ብለዋል።
የዜጎችን ሁለተናዊ ህይወት የመቀየር ስራ በመንግስት በጀት ብቻ እንደማይሳካ ገብቶን “መስጠት አያጎድልም “በማለት በርካታ ልበ ቀና ባለሀብቶችን በማስተባበር በመስራት የበርካቶችን ህይወት መቀየር ችለናል ነው ያሉት ከንቲባዋ።
ለዚህም የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አመራሮች እና ሰራተኞችን በነዋሪዎች እና በራሳቸው ስም አመስግነዋል።