የ2016 በጀት ዓመት ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ የሚሞክሩ ፀረ ሰላም ኃይሎችን ዕቅድ ማክሸፍ የተቻለበት ዓመት መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው የአዲስ አበባ ፖሊስ በተጠናቀቀው በጀት አመት ያከናወናቸው ተግባራትን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በተጠናቀቀው በጀት አመት በከተማዋ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር በናሁሰናይ የተመራ 38 የሽብር ቡድን አባላት መያዙን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የሽብር ቡድኑ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች እና የህዝብ ትራንስፖርቶች ላይ ፈንጂዎችን ለማፈንዳት አቅዶ ወደ ከተማዋ ገብቶ እንደነበርም በመግለጫቸው ዘርዝረዋል፡፡
ከተለያዩ የፀጥታ አካላት ጋር በተሰራ ስራ ይህንን ሴራ ማክሸፍ መቻሉን እና የሽብር ቡድኑ አባላት በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
የራይድ ሹፌሮች ላይ የግድያ ወንጀል የፈፀሙ አካላት ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተሰርቷል ብለዋል ኮሚሸነሩ።
የተጠናቀቀው የበጀት አመት በተለያዩ ጊዜያት ወንጀል ሲፈፅሙ በተገኙ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ በመመስረት ከ5 ሺ በላይ መዝገቦች ውሳኔ ያገኙበት መሆኑንም በመግለጫው አንስተዋል።
በሌሉበት የተፈረደባቸው አካላት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ በሌሉበት ከ1 እሰከ 17 አመት የተፈረደባቸውን በማፈላለግ 563 ወንጀለኞችን ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ በሞባይል ቅሚያ፣ የመኪና እቃዎች ስርቆት እና በጥቁር ገበያ ውስጥ የተሰማሩ በርካታ አካላት መያዛቸውን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
በተጠናቀቀው በጀት አመት በከተማው ውስጥ የተቃጡ የሽብር ሴራዎችን የከሸፈበት በጦር መሳሪያ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ አካላት በህግ ተጠያቂ የተደረገበት አመት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በተጨማሪም የስነ ምግባር ጉድለት የታየባቸው፤ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈፅሙ በተገኙ 490 የፖሊስ አባላትን ከስራና ከደሞዝ በማገድ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉን ጠቅሰዋል።
አዲስ አበባ የጀመረችውን የብልፅግና ጉዞ ለማስቀጠል እንዲሁም ለነዋሪዎቹ ምቹ እና ሰላሟ የተጠበቀ ለማድረግ የአዲስ አበባ ፓሊስ ለሊት እና ቀን 24 ሰአት በሙሉ ህዝቡን እያገለገለ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የማህበረሰብ አቀፍ ማዕከላት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፤ በተጠናቀቀው በጀት አመት ነዋሪው የከተማውን ሰላም ለማስጠበቅ ላከናወናቸው ተግባራት ምስጋና አቅርበዋል።
በወይንሸት ደጀኔ