"መንግስት እና ህዝብን የሚያገናኙ በርካታ ውይይቶች አካሂደናል" - የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ

1 Mon Ago 484
"መንግስት እና ህዝብን የሚያገናኙ በርካታ ውይይቶች አካሂደናል" - የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ

"መንግስት እና ህዝብን የሚያገናኙ በርካታ ውይይቶች አካሂደናል" - የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ

"ጥያቄዎች እና ቅሬታዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሊፈቱ ይገባል፤ለዚህም መንግስት ሁሌም ዝግጁ ነው " - በኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ

******************

በአማራ ክልል ያለውን ያለመረጋጋት ለመግታት በክልሉ የተለያዩ ውይይቶች ከነዋሪዎች ጋር መደረጋቸውን የክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ እና የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ገለልተኛ የሆኑ አካላት በነፃነት በመሳተፍ ችግሮች ላይ መምከራቸውንም አንስተዋል፡፡

መንግስት እና ህዝብን የሚያገናኙ ውይይቶችን አካሂደናል ያሉት ኃላፊው፤ ክልሉ እንዳይረጋጋ ያደረጉ ምክንያቶች መለየታቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

በተለያየ ጊዜ አብዛኛውን የክልሉ ነዋሪዎችን ማወያየት መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ የሚነሱ ጥያቄዎች የክልሉ ብቻ ሳይሆኑ የፌደራል መንግስትም በእኔነት የሚመለከታቸው ጉዳዮች ናቸው ያሉት ኃላፊው፤ በዚህም መንግስት ችግሮችን ያለምንም ደም መፋሰስ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ክልሉ በገባበት የጸጥታ ችግር እየተጎዳ ያለውን የማህበረሰብ ክፍል እፎይታ ለመስጠት በተደረገ ውይይት ማጠናቀቂያ ላይ ባለ አስር ነጥብ የአቋም መግለጫ መቀመጡ የሚታወስ ነው ብለዋል፡፡

መንግስት በተለያዩ ጊዜያቶች ሰላም ለማምጣት እና ለመደራደር "መቼም፤ በየትኛውም ቦታ" ዝግጁ ነኝ ሲል ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቷል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል በሰሜኑ የሀገሪቷ ክፍል የተፈጠረውን ያለመረጋጋት ለመግታት መንግስት ያቀረበው የሰላም ጥሪ ወቅቱን የጠበቀ ነው የሚሉት በኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ሰላም ለማስፈን በመንግስት መዋቅር ውስጥ በተለያዩ ደረጃ የሚገኙ አመራሮች ጥሪ ማቅረባቸውን በማስታወስ፤ ይህም መንግስት ለሰላም መስፈን ያለውን ፍላጎት እና ቁርጠኛነት ያሳየበት ነው ብለዋል፡፡

የፕሪቶሪያው ስምምነት አንዱ ማሳያ እንደሆነም ነው የሚገልጹት፡፡

ኢትዮጵያ ለሰላም መስፈን ዘብ ከሚቆሙት ቀዳሚ መሆኗን በመግለፅ ፤ ከሀገር ባለፈ በቀጠናው የሚፈጠሩ ችግሮችን በመፍታት ሂደት ውስጥ በኮንጎ፣ ሶማሊያ እና ሱዳን የራሷን ወታደሮች በመሰዋት የበኩሏን የተወጣች ሀገር ናት ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

የፈረሱ ሀገራት የጦርነት ጉዳት እና መዳረሻ ምን እንደሆነ ማሳያ ናቸው በማለት፤ መንግስት ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡም ሰላም እና መረጋጋትን ይሻል ይላሉ፡፡

ህዝብ በሰላም ወቶ በሰላም መግባትን ሲሻ መንግስት ይህን የማስከበር ሚናውን የመወጣት ኃላፊነት አለበት ያሉት የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ፤ ይህ እንዳይሆን በኃይል እና በተዛባ ትርክት የመላው ኢትዮጵያውያንን ፍላጎት የሚጋፉ  አካላት ድርጊት አግባብ እንዳልሆነም ነው የገለፁት፡፡

የጥቄዎች እና ችግሮች መፍቻ ውይይት እንደሆነ በመግለጽ፤ በዴሞክራሲ የተመረጠ መንግስትን አልቀበልም ብሎ በጠብመንጃ መንቀሳቀስ አግባብ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

መንግስት ሰላም በማስጠበቅ አስገዳጅነት ወደ ጦርነት መግባቱን ገልፀው፤ የተደረገው የሰላም ጥሪ እንዳልረፈደ ይናገራሉ፡፡

ጥያቄዎች እና ቅሬታዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሊፈቱ ይገባል ፤ ለዚህም መንግስት ሁሌም ዝግጁ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የሰላም ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ምላሽ ከሰጡባቸው ሃሳቦች አንዱ መሆኑም የሚታወስ ነው፡፡

"ጦርነት መጀመር በጣም ቀላል ነገር ነው፤ ከኪስ ውስጥ በሚወጣ ትንሽ ክብሪት እሳት እንደሚለኮሰው ነው፤ በተለኮሰው መጠን ልክ አይጠፋም፤ ማገዶ አውድሞ፣ ቤት አንድዶ ነው ሚጠፋው፤ እሳት መለኮስና ማጥፋት እኩል አደለም፤ ለዚህ ነው በተደጋጋሚ የጥይት ድምጽ ይብቃን የምንለው" ሲሉ የጦርነትን አስከፊነት  መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በአፎሚያ ክበበው

 

 

 

 

 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top