የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በ2017 ዓ.ም የቤት ለቤት የፓስፖርት አገልግሎት እንደሚጀምር አስታውቋል።
አዳዲስ የአሰራር ማዕቀፎች ተግባራዊ እንደሚደረጉ እና በተለይም ሕጋዊ መረጃዎችን ላሟሉ ዜጎች አስፈላጊውን ክፍያ በመክፈል የቤት ለቤት አገልግሎት ለማስጀመር በዕቅድ መያዙ ተገልጿል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በሰጠው መግለጫ፤ በበጀት ዓመቱ 1.1 ሚሊዮን ፓስፖርት ለተገልጋዮች ማድረሱን የአገልግሎቱ ዋና ዳሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ተናግረዋል።
በዘንድሮው ዓመት ለትውልደ ኢትዮጵያውያን 51 ሺህ መታወቂያ መስጠት መቻሉም ተመላክቷል።
ተቋሙ በቀን ፓስፖርት የማተም አቅምሙን ከ2 ሺህ ወደ 14 ሺህ ከፍ አድርጓል ተብሏል።
ተቋሙ እየሰራ ካለው የሪፎርም ሥራ ጎን ለጎን ባደረገው ሥራ 620 ሺህ የቪዛ አገልግሎት ለውጭ ዜጎች መስጠት ተችሏል።
ተቋሙ ከአገልግሎት ክፍያ 14.7 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ ችሏል።
ከነሐሴ ወር ጀምሮ አዲስ የአገልግሎት ክፍያ ተመን ተግባራዊ እንደሚያደርግም አስታውቋል።
አንድ ዓመት ከአምስት ወር ያክል ፓስፖርት የመስጠት አገልግሎት ተቋርጦ የነበረ በመሆኑ፤ በበጀት ዓመቱ የተጠራቀመ ፍላጎት እንዲቀረፍ ተደርጓል ተብሏል።
ዘመናዊ አሰራርን ተግባራዊ ለማድርግ የሚያስችል መስሪያ ቤት 74 በመቶ መጠናቀቁን የገለፁት ዋና ዳሬክተሯ፤ በአዲሱ ዓመት ወደዛው እንደሚዛወሩ ተናግረዋል።