አረንጓዴ አሻራ ለኢትዮያውያን እንደ ባህል እስኪቆጠር ተግተን በመሥራት አረንጓዴ የለበሰች ኢትዮጵያን እውን አናደርጋለን፡- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

19 Days Ago
አረንጓዴ አሻራ ለኢትዮያውያን እንደ ባህል እስኪቆጠር ተግተን በመሥራት አረንጓዴ የለበሰች ኢትዮጵያን እውን አናደርጋለን፡- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አረንጓዴ አሻራ ለኢትዮያውያን እንደ ባህል እስኪቆጠር ተግተን በመሥራት አረንጓዴ የለበሰች ኢትዮጵያን እውን አናደርጋለን ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
 
የአገልግሎቱ ሙሉ መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል፡-
 
አረንጓዴ አሻራ ለኢትዮያውያን እንደ ባህል እስኪቆጠር ተግተን በመሥራት አረንጓዴ የለበሰች ኢትዮጵያን እውን አናደርጋለን!
 
ባለፉት ዓመታት በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች በመጀመሪያዉ ምዕራፍ ከ32 ቢሊየን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን የተተከሉት ችግኞችም በዘርፉ ሙያተኞች በተደረጉት ክትትል 90% ለመፅደቅ ችለዋል፡፡
 
የተፈጥሮ ሃብትና የሕይወታዊ ሃብት ጥበቃ ሥራ ሲጠናከርና ተከታታይነት ባለው መንገድ ሲሰራ ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ነጻ የሆነና መልካምድራዊ አቀማመጥን መሰረት ያደረገ አካባቢያዊ የአየር ንብረት እንዲኖር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ እድል ይሰጣል፡፡
 
ከዚህ በተቃራኒ የተራቆተ መሬትና አከባቢ በኢኮኖሚ፤ በማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚኖረው ተጽዕኖ ቀላይ አይሆንም፡፡ የልምላሜ ስነ ልቦናዊ፤ ሠላም፤ ደስታ፤ ፍቅርና ተስፋዎችም ይሰጣሉ፡፡
 
በመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመላ ሃገሪቱ በተተከሉ ችግኞች ቀደም ሲል ተራቁተው የነበሩና የአፈር መሸርሸር አጋጥሟቸው የነበሩ አከባቢዎች በአሁኑ ወቅት ወደ ቀድሞ ገጽታቸው እየተመለሱና መሬቱም እያገገመ መሆኑን የግብርና ባለሙያዎች ምስክርነታቸውን እየሰጡ ነው፡፡የአረንጓዴ አሻራ ሥራችን በተለያዩ ዘርፎች ውጤቶችን እያሳየን ነው፡፡
 
ተደጋጋሚ ድርቅ ሲያጠቃቸው የነበሩ አካባቢዎች ዝናብ ማግኘት ጀምረዋል፣ የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ ተችሏል፣ የደረቁ ምንጮችና ሀይቆች እንደገና ቀድሞ ወደ ነበሩበት መመለስ ችለዋል፣ ለበጋና የመኽር እርሻ ተስማሚ የሆነ ዝናብ ማግኘት ተችሏል፡፡ከሥራ እድል ፈጠራነት አንጻር ለእንስሳት መኖነት፤ ለንብ ማነብ ፤ ለካርቦን ሽያጭና ለጎረቤት ሀገራት መልካም ጉርብትና እና የዲፕሎማሲ ግንኝነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
 
በዘንድሮ 2016/17 በ132 ሺህ 144 ችግኝ ጣቢያዎች ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብሩ ችግኝ ተዘጋጅቶ 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የቅድመ-ተከላ ዝግጅቶች በሁሉም አካባቢዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ 25 በመቶ የሚሆነው በአባይ ተፋሰሶች የሚተከል ይሆናል፡፡ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ዝግጅትና ተከላ ለበርካታ ወጣቶችና ሴቶች ሰፊ የስራ እድል እየፈጠ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
 
በዘንድሮው የችግኝ ተከላ በ6 ሺህ 200 ተፋሰሶች የስነ-አካላዊ ስራ በመስራት በስነ-ህይወታዊ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይ ለተከላ የተዘጋጁ ችግኞች ዘርፈ ብዙ ገቢ የሚየስገኙ አትክልትና ፍራፍሬ፤ ጥምር ደን፤ ለከተሜነት ዉበት የሚዉሉ እና ለደን የሚዉሉ ናቸዉ፡፡ ለሁለተኛው አረንጓዴ አሻራ ሁለተኛ ዓመት የአረንጓድ አሻራ ስኬት የሁላችንም ተሳትፎና ዝግጁነት ከወዲሁ ይጠበቃል፡፡
 
አረንጓዴ አሻራ ለኢትዮያዊያን እንደ ባህል እስኪቆጠር ተግተን በመሥራት አረንጓዴ የለበሰች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በጋራ ልንቆም ይገባል፡፡
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top