የኒጀር ወታደራዊ ጁንታ ፕሬዚዳንት ባዙምን እንዲለቅቅ ናይጄሪያ ጠየቀች

2 Mons Ago
የኒጀር ወታደራዊ ጁንታ ፕሬዚዳንት ባዙምን እንዲለቅቅ ናይጄሪያ ጠየቀች
ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ባዙም (ፎቶ - ፋይል)

የኒጀር ወታደራዊ ጁንታ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ባዙምን እንድሊቅቅ እና ወደ ሦስተኛ ሀገር እንዲሄዱ እንዲፈቅድ ናይጄሪያ ጥያቄ አቅርባለች።

ናይጄሪይ የወቅቱ የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) ሊቀ መንበር ነች።

የሐምሌውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ፣ ኢኮዋስ በኒጀር ላይ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል።

ኢኮዋስ ባዙም ወደ ሥልጣናቸው እንዲመለሱ ጥሪ ቢያቀርብም፣ ወታደራዊ ጁንታው በአንፃሩ “ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ እስከ ሦስት ዓመት ያስፈልገኛል” በሚል ባዙምን አግቶ ቆይቷል።

የናይጄሪያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዩሱፍ ቱጋር፣ “ፕሬዚዳንት ባዙም ኒጀርን ለቅቀው መውጣት እንዲችሉ ጥያቄአችንን አቅርበናል” ሲሉ ለሀገር ውስጥ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ተናግረዋል።

“ወደ ሦስተኛ ሀገር እንዲሄዱ ከተደረገ በኋላ፣ ማዕቀቡን ስለማንሳት እንነጋገራለን” ብለዋል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ።

እንደ ቪኦኤ ዘገባ የኢኮዋስ መሪዎች በናይጄሪያ ጉባኤ እንደሚቀመጡ ባለፈው ሳምንት ተነግሯል።

በጉባኤው ባለፉት ሦስት ዓመታት በማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ጊኒ እና ኒጀር መፈንቅለ መንግሥት ስላስተናገደው ቀጠና ይወያያሉ ተብሏል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top