ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር እና በተለያዩ መስኮች ትብብራቸውን ለማጎልበት የፓርላማ ልዑካን የልምድ ልውውጥ ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
ውይይቱ የተደረገው በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር በዛሬው ዕለት በፓኪስታን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ ሊቀመንበር ሙሐመድ ሳዲቅ ሳንጅራኒ ጋር በመከሩበት ወቅት መሆኑን ‘ኡርዱ ፖይንት’ የተሰኘው የፓኪስታን የዜና አውታር ዘግቧል።
በውይይታቸውም ሁለቱ አካላት በኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የሁለትዮሽ፣ ቀጠናዊ እና ባለብዙ ወገን ትብብር ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ተገልጿል።
በኢትዮጵያ እና ፓኪስታን መካከል ያለው የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ አነስተኛ ነበር ያሉት አምባሳደር ጀማል በከር፣ የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚያዊ እና የንግድ ትሥሥር በማጎልበት የሁለትዮሽ ንግድን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል።
ፓኪስታን በምታራምደው አፍሪካን የማሳተፍ ፖሊሲዋ የኢትዮጵያ አስፈላጊነት የጎላ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ፣ የኢትዮጵያ ገበያ ለፓኪስታን የንግድ ማኅበረሰብ ትርፋማ የንግድ፣ የቢዝነስ እና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን አቅርቧል ብለዋል።
የሰው ዘር መገኛ እና የአፍሪካ አህጉር መግቢያ የሆነችውን ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ አምባሳደር ጀማል በከር ለሳንጅራኒ ግብዣ አቅርበዋል።
የፓኪስታን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊቀመንበሩ ሙሐመድ ሳዲቅ ሳንጅራኒ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ አምባሳደሩ ላደረጉላቸው ግብዣ ምስጋና አቅርበዋል።
የፓርላማ ልዑካን የልምድ ልውውጥ ማድረግ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት እንደሚያጠናክር ጠቁመው፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው በጋራ ታሪክ፣ በጋራ ጥቅም እና በዓለም አቀፍ መድረኮች በጋራ መደጋገፍ ላይ የተመሠረተው ጠንካራ ትሥሥር ጠቀሜታው ትልቅ መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ፓኪስታንን ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከመላው አፍሪካ ጋር የሚያገናኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ካራቺ በረራ እንዲጀምር በማድረጉም ለኢትዮጵያ መንግሥት ምስጋና አቅርበዋል።