“አዞው” በሚል ቅፅል ስም የሚታወቁት የዚምባብዌ መሪ ዳግም አሸነፉ

1 Yr Ago 727
“አዞው” በሚል ቅፅል ስም የሚታወቁት የዚምባብዌ መሪ ዳግም አሸነፉ

 

 በአስደናቂ መልክዓ ምድሯ፣ በተፈጥሮ ሀብቷ የምትታወቀው ዚምባብዌ በደቡባዊ የአፍሪካ ክፍል የምትገኝ ወደብ አልባ ሀገር ናት። በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የዋጋ ንረት፣ ሥራ አጥነት እና አልፎ አልፎ የሚከሰት ድርቅ የሚያጠቃት ዚምባብዌ በፖለቲካው በኩልም ቢሆን ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፋለች።

 ዚምባብዌ ከቅኝ ግዛት ነፃነቷን ካገኘች ጊዜ ጀምሮ በታሪኳ ሁለት መሪዎች የተመለከተች ሲሆን፤ ሀገሪቱ ዘንድሮው ባደረገችው ምርጫም ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ለ2ኛ ጊዜ የሀገሪቱ መሪ እንዲሆኑ መርጣለች።

 ኤመርሰን ዳምቡድዞ ምናንጋግዋ (አዞው) ከ1980ዎቹ ጀምሮ የዚምባቡዌ ቀንደኛ ፖለቲከኛ የነበሩ ሲሆን እ.አ.አ ከ2017 ጀምሮ የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።

 ዚምባብዌ ከቅኝ ግዛት ተላቅቃ ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ ምናንጋግዋ በቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ የመሪነት ዘመን የተለያዩ ከፍተኛ የካቢኔ ቦታዎችን ይዘው የነበረ ሲሆን እ.አ.አ. ከ1980 እስከ 1988 የሀገሪቱ የመጀመሪያው የደኅንነት ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

 ምናንጋግዋ ከመፈንቅለ መንግሥቱ በፊት በነበሩት ጊዜያት ከሙጋቤ የቅርብ ሹማምንቶች ውስጥ አንዱ የነበሩ ሲሆኑ በምክትል ፕሬዚዳንትነት፣ በፀጥታ ጥበቃ ሚኒስትርነት እና በሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ቦታዎች ላይ አገልግለዋል።

 በታኅሣሥ 10 ቀን 2014 ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ምናንጋግዋን የዚምባብዌ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አድርገው የሾሟቸው ሲሆን፣ ብዙም ሳይቆይ በአንዳንድ የፕሬዚዳንታዊ ሥራዎች ላይ ውክልና ተሰጥቷቸው እንደሠሩ እና ጥር 11 ቀን 2016 ሙጋቤ የዓመት እረፍት ላይ በነበሩበት ወቅት ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሆነው ማገልገላቸው ይነገራል።

 የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት የረዥም ጊዜ አጋር የሆኑት ምናንጋግዋ እስከ ኅዳር 2017 የሙጋቤ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነውም አገልግለዋል።

    የሙጋቤ እና የምናንጋግዋ ግንኙነት ከወዳጅነት ወደ ጠላትነት መቀየሩ

 ምናንጋግዋ የሮበርት ሙጋቤ የቅርብ ሰው ሆነው ለዓመታት ከቆዩ በኋላ በመካከላቸው በተፈጠረ ችግር ምከንያት ግንኙነታቸው በእጅጉ እየሻከረ መጣ። የምናንጋግዋ ሁናቴ ያልጣማቸው እና በሥልጣናቸው ቀልድ የማያውቁት ሙጋቤ የረዥም ጊዜ አጋራቸውን እና ምክትላቸውን፤ አክብሮት እና ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ፈፅመዋል በማለት ከምክትል ፕሬዚዳንትነት አሰናበቱ።

 እ.አ.አ ኅዳር 8 ቀን 2017፣ ምናንጋግዋ ከምክትል ፕሬዚዳንትነት ከተሰናበቱ ከሁለት ቀናት በኋላ ምናንጋግዋ በራሳቸው እና በቤተሰባቸው ላይ ከሚደርስባቸው "የማያቋርጥ ዛቻ" ለማምለጥ በመጀመሪያ ወደ ሞዛምቢክ ከዚያም ወደ ደቡብ አፍሪካ ተሰደዱ።

 ይህ ከሆነ ከአንድ ሳምንት በኋላ፣ ኅዳር 14 ቀን 2017 የዚምባብዌ ወታደራዊ አካላት በዋና ከተማዋ በሐራሬ የሚገኘውን የዚምባብዌ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ZBC) እና የከተማዋን ቁልፍ ቦታዎች ተቆጣጠሩ። በማግስቱ ሜጀር ጄኔራል ሲቡሲሶ ሞዮ የዚምባብዌ መከላከያ ሠራዊትን በመወከል በዜድቢሲ የመንግሥት ብሮድካስት ላይ በቀጥታ ስርጭት መግለጫ ሰጡ።

 በመግለጫውም ሞዮ ወታደራዊ ኃይሉ ሥልጣኑን ለራሱ እንደማይረከብ እና ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ደህና መሆናቸውን ተናግረው፣ ወታደራዊ ኃይሉ ለሀገሪቱ ችግሮች ተጠያቂ ናቸው ያላቸው ወንጀለኞች ላይ እያነጣጠረ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ተናገሩ።

 ኅዳር 19 ቀን 2017 ፕሬዚዳንት ሙጋቤ፣ ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ እና 20 ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከዛኑ-ፒኤፍ ፓርቲ ተባረሩ። በወቅቱ ደቡብ አፍሪካ የነበሩት ምናንጋግዋ የፓርቲው አዲስ መሪ ሆነውም ተመረጡ።

 ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ላይ የክስ ሂደት ከመጀመሩ በፊት በወታደራዊው ኃይል ሥልጣን እንዲለቁ ተጠይቀዋል። የሥልጣን መንበራቸው ላይ ሙጥኝ ብለው ዚምባብዌን ለ37 ዓመታት የመሩት ሮበርት ሙጋቤ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ሲጠየቁ "እግዚአብሔር እንደሾመኝ እግዚአብሔር ብቻ ነው የሚያወርደኝ"  በማለት አሻፈረኝ አሉ። የወታደራዊው ኃይሉ ሥልጣን እንዲለቁ በተደጋጋሚ ጠይቋቸው ፍቃደኛ ሳይሆኑ የቆዩት ሙጋቤ፤ በመጨረሻ ግን ከመከሰሳቸው በፊት ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ተገደዱ።

 ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲም ወዲያው ምናንጋግዋን ተተኪ አድርጎ በመሾም በ48 ሰዓታት ውስጥ ሥልጣን እንደሚረከቡ አስታወቀ። ምናንጋግዋም ብዙም ሳይቆዩ ኅዳር 22 ቀን 2017 በስደት ከሄዱባት ደቡብ አፍሪካ ወደ ዚምባብዌ ተመልሰው በመምጣት ኅዳር 24 ቀን 2017 የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ፈፀሙ።

 ምናንጋግዋ እ.አ.አ. በ2017 ከተካሄደው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በኋላ ሙጋቤን በፕሬዚዳንትነት ተክተው፣ በ2018 ተካሂዶ የነበረውን አጨቃጫቂ ምርጫ አሸንፈው ፕሬዚዳንት ለመሆን በቅተዋል።

 በአንድ ወቅት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ጠባቂ እና ደጋፊ የነበሩት ምናንጋግዋ 15 ሚሊዮን ለሚሆኑት የሀገሪቱ ሕዝቦች ነፃነት እና ዲሞክራሲ ለማስፈን ብሎም በሙጋቤ የሥልጣን ዘመን ከነበረው የጭቆና እና የገለልተኝነት ዘመን ሕዝቡን ነፃ ለማውጣት ቃል ቢገቡም፣ ሥልጣን ላይ በቆዩበት ጊዜ ትንሽ እንኳን የለውጥ ምልክት አልታየም። ይልቁንም በቀድሞው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ኮቴ ይራመዳሉ ተብለው ይተቻሉ።

 ምናንጋግዋ የለውጥ ብልጭታ እንኳን ማስፈንጠቅ ላለመቻላቸው እንደምክንያት የተወሰደው ወደ ሥልጣን የመጡበት መንገድ ሲሆን በ1970ዎቹ ደም አፋሳሽ የነፃነት ጦርነት ወቅት ጠባቂ ሆኖ ከማገልገል ጀምሮ በ1980ዎቹ እና 1990ዎቹ የካቢኔ ሚኒስትር እስከመሆን በመቀጠልም ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው በወዳጃቸው በሮበርት ሙጋቤ ከመሾም አንሥቶ የፖለቲካ ጠላቶች ሆነው ከሹመታቸው እስከተባረሩበት ድረስ የነበረው ሂደት እንደምክንያት ይጠቀሳል።

 በሌላ በኩል የቀድሞው የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ማንኛውንም ተቃዋሚ በግልጽ በመጨቆን እና በምዕራቡ ዓለም ላይ በሚያሰሙት የጩኸት ንግግራቸው ሲታወቁ ምናንጋግዋ ግን ለስላሳ የሆነ የግንኙነት እና የንግግር ዘዴን በመጠቀም ይታወቃሉ።

 የ80 ዓመቱ አዛውንት ምናንጋግዋ በሳምንቱ አጋማሽ በተካሄደው ምርጫ አብላጫውን ድምፅ በማግኘት ለ2ኛ ጊዜ የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት መሆን ችለዋል። 

 የዚምባብዌ የምርጫ ኮሚሽን ይፋ ባደረገው ውጤት መሠረት የኤመርሰን ምናንጋግዋ ለ2ኛ ጊዜ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ድምፅ ከሰጡ መራጮች መካከል የ52.6 በመቶን ይሁንታ በማግኘታቸው ሲሆን፤ የኤመርሰን መናንጋግዋ ጠንካራ ተቀናቃኙ የዜጎች ጥምረት ለዘላቂ ለውጥ የፓለቲካ ፓርቲ መሪ ኔልሰን ቻሚሳ በበኩላቸው የ44 በመቶ የመራጮችን ድምፅ አግኝተዋል።

 ዘንድሮ በተካሄደው ምርጫ ተወዳዳሪ የነበረው የዜጎች ጥምረት ለለውጥ ፓርቲ (ሲሲሲ) ግልፅ የሆነ ማጭበርበር የታየበት ምርጫ በማለት ውጤቱን እንደማይቀበል ያሳወቀ ሲሆን፣ “ደጋፊዎቼ በገዥው ፓርቲ ጥቃት እና ማስፈራራት ደርሶባቸዋል፤ በፖሊስ ተይዘው ለእንግልት ተዳርገዋል” ሲልም ከሷል።

 የምርጫ ሂደቱ እና ውጤቱ በአንዳነዶች ፍትሐዊ እና ነፃ ነው ቢባልም ሌሎች ደግሞ ምርጫው የተጭበረበረ ነው ሲሉ ኮንነዋል። ይሁንና የዚምባብዌ ምርጫ ቦርድ ውጤቱን ማፅደቁን ተከትሎ ገዢው ዛኑ-ፒኤፍ ፓርቲ የ43 ዓመታት የሥልጣን ቆይታው ሲራዘም፣ ምናንጋግዋም ለሁለተኛ ጊዜ በፕሬዚዳንትነት ተመርጠዋል። የመረጃው ምንጮቻችን ቢቢሲ፣ ሬውተርስ፣ አሶሼትድ ፕሬስ እና አለም ባንክ ናቸው።

 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top