የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ባለመድረሱ ምክንያት ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን ክልሎች አስታወቁ

1 Yr Ago 830
የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ባለመድረሱ ምክንያት ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን ክልሎች አስታወቁ

የ2015/16 ዓ.ም ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት በመጓተቱ እና በወቅቱ ባለመድረሱ ምክንያት ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን የአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮዎች አስታወቁ።

የማዳበሪያ ፍላጎት እና አቅርቦት አለመመጣጠንም ተግዳሮት እንደሆነባቸው ነው ክልሎቹ የገለጹት።

ግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ፣ የ2015/16 ዓ.ም ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያን በፍጥነት ለማድረስ እየሰራሁ ነው ብሏል።

በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ከበደ ላቀው ለኢቢሲ ሳይበር እንደገለጹት፣ 12.8 ሚሊዮን ኩንታል የማዳበሪያ ግዢ ተፈጽሞ 7.5 ሚሊዮን ኩንታል ጂቡቲ ወደብ ደርሷል።

ጂቡቲ ወደብ ከደረሰው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥም 6.6 ሚሊዮን ኩንታል ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዞ ሙሉ በሙሉ ወደ ክልሎች እንዲሰራጭ ተደርጓል ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ሁሉንም የማጓጓዣ ዘዴዎች በመጠቀም ወደብ የደረሰውን ማዳበሪያ በማጓጓዝ ላይ መሆኑን አቶ ከበደ ገልጸዋል።

በሁሉም ደረጃ ያለው አመራርም በፍጥነት በማጓጓዝ እና ሥርጭቱን በማቀላጠፍ ላይ እየተረባረበ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ከበደ፣ ክልሎችም የደረሳቸውን ማዳበሪያ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የሰብል ዓይነቶች ከግምት በማስገባት በፍትሃዊነት ማሰራጨት አለባቸው ብለዋል።

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ እንዳሻው ጀማነህ በበኩላቸው፣ በ2015/16 ምርት ዘመን የክልሉ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት 9 ሚሊዮን ኩንታል ነበር ብለዋል።

ነገር ግን እስካሁን የደረሰው 3 ሚሊዮን ኩንታል መሆኑን ጠቅሰው፣ የከረመውን ጨምሮ ወደ 4 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱን ተናግረዋል። የፍላጎት እና አቅርቦት አለመመጣጠንም ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሥርጭቱ በህብረት ሥራ ማኅበራት በኩል እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት አቶ እንዳሻው፣ ምንም ክፍተት ሳይፈጠር ቅድሚያ ለሚዘሩት የሰብል ዓይነቶችን ከግምት በማስገባት ለማሰራጨት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ህዘብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ አንተነህ ሰዋገኝ፣ የክልሉ የ2015/16 ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት 9.5 ሚሊዮን እንደነበረ ገልጸው፣ የተፈቀደው ግን 5.3 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ነው ብለዋል።

ከተፈቀደው ውስጥም 2.5 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያም በክልሉ ደርሶ መሰራጨቱን ገልጸዋል። 250 ሺህ ኩንታል የከረመ ማዳበሪያም ሥርጭቱ ውስጥ መካተቱንም አስታውሰዋል።

ቢሮው ቅድሚያ ለሚዘሩት ሰብሎች ትኩረት ሰጥቶ ሥርጭቱን እያከናወነ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አንተነህ፣ በዚህም 1.2 ሚሊዮን ኩንታል ቅድሚያ ተሰጥቶ ተሰራጭቷል ብለዋል።

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top