ጥምረቱ በቅርቡ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሰጡትን ያልተገባ አስተያየት በመቃወም መግለጫ አወጣ

1 Yr Ago
ጥምረቱ በቅርቡ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሰጡትን ያልተገባ አስተያየት በመቃወም መግለጫ አወጣ
አስራ ሶስት ተቋማትን የያዘው ዓለም አቀፍ የትብብር ጥምረት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቅርቡ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሰጡትን ያልተገባ አስተያየት በመቃወም መግለጫ አወጣ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብንና የውሀ ሀብት ፕሮጀክቶች አስተዳደርን ለመደገፍ የተቋቋመው ጥምረቱ መግለጫውን ያወጣው በቅርቡ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አራተኛ ሙሌት መቃረቡን ተከትሎ ‘ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው’ በማለት የሰጡትን ያልተገባ አስተያየት በመቃወም ነው።
ጥምረቱ በመግለጫው ተከታታይ የግብጽ መንግስታት ተመሳሳይ የጦርነት ፍላጎትን የሚያንጸባርቁ ዛቻዎችን በላይኞቹ ተፋሰስ ሀገሮች ላይ በማቅረብ እንደሚታወቁ አስታውሶ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቅርቡ የሰጡት ያልተገባ አስተያየትም ከተለመደውና ምክንያታዊነት ከሚጎድለው የግብጽ መንግስት አካሄድ ያልተለየ መሆኑን አስገንዝቧል።
ጥምረቱ አክሎም የላይኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ግብጽ ምንም አስተዋጽኦ የማታበረክትበትን ውሀ በበላይነት ለመቆጣጠር የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንድታቆምና በህግ እንድትገዛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሶ፣ በግብጽ በኩል ራሷን እንደ አንድ የተፋሰሱ ሀገርና የዕኩል መብቶች ተጋሪ የማየት ችግር አለ ብሏል።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በተፈራረሙት የመርሆዎች ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታና ሙሌት ጎን ለጎን ማካሄድ እንደምትችል ያስታወሰው መግለጫው፣ በዚሁ ስምምነት መሰረት ሶስት ጊዜ በተካሄደው ሙሌት ምንም አይነት ጉልህ ጉዳት በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ አልተፈጠረም ብሏል።
አራተኛው ሙሌት በዕቅዱ መሰረት እንዳይካሄድ ለማስተጓጎልና የዓለም ውሀ ፎረም ተሳታፊዎችን ለማሳሳት በማሰብ ሚኒስትሩ አስተያየቱን መስጠታቸው የግብጽ መንግስትን ቀቢጸ ተስፋ እንቅስቃሴ የሚያሳይ እርምጃ ነው ብሏል።
ጥምረቱ በመጨረሻም የግብጽ መንግስት በአባይ ወንዝ ላይ አለኝ ብሎ የሚያስበውን የበላይነት ስሜት በመተው ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ተቀራርቦ እንዲሰራና የአባይ ውሀ አሁን ባለውም ሆነ በቀጣዩ ትውልድ በፍትሐዊነት፣ በምክንያታዊነትና ዘላቂ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል አዎንታዊ ሚና እንዲጫወት ማሳሰቡን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት መረጃ ያመለክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top