አረንጓዴ አሻራ የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ በፍራፍሬ ልማት የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ መሳሪያ ሆኗል፡- ግብርና ሚኒስቴር

4 Days Ago 157
አረንጓዴ አሻራ የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ በፍራፍሬ ልማት የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ መሳሪያ ሆኗል፡- ግብርና ሚኒስቴር
አረንጓዴ አሻራ የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ በፍራፍሬ ልማት የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ መሳሪያ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ።
 
14ኛው ዓለም አቀፍ የደን ቀን "ደንና ምግብ" በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ነው።
 
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በመድረኩ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በመሬት አቀማመጥ፣ በተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም ተስማሚ የአየር ንብረት የታደለች ሀገር ናት።
 
ደንን መሰረት ባላደረገ የኢኮኖሚ ዘይቤ ምክንያት ከዚህ ቀደም የከፋ የደን መመናመን እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ይህንን የሚያስተካክል ፖሊሲ ቀርጻ በመተግበር ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።
 
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ በፍራፍሬ ልማት የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ መሳሪያ መሆኑን አንስተዋል።
 
በተጨማሪም ከምግብ ፍጆታ ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ምንጭ መሆኑንና በስራ እድል ፈጠራም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።
 
ለ2017 የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እስካሁን 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
 
መንግስት ከየትኛውም ጊዜ በላይ ለተፈጥሮ ጥበቃ እና ለአረንጓዴ ልማት ልዩ ትኩረት መስጠቱን አመላክተዋል።
 
የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም በበኩላቸው፤ በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ሀብት መሆኑን ጠቅሰው፤ በደን ላይ የሚደርስ ጉዳት ዘላቂ ልማትን ወደ ኋላ የሚቀለብስ መሆኑንም ጠቁመዋል።
 
የኢትዮጵያ ደን ልማትም ዘርፉን በእውቀት እና በክህሎት ለመምራት ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
በመርሀ-ግብሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ሙባረክ ኤልያስ፣ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ እንዲሁም የፌደራል እና የክልል የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top