የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስርቆት ማህበረሰቡ የሚፈልገውን የማይቋረጥ አገልግሎት ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት እያስተጓጎለ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
በቂ ኃይል ለማቅረብ ብሎም ለማዳረስ እየተሰራ ቢሆንም የመሰረተ ልማት ስርቆቱ አመርቂ ውጤት እንዳይመጣ ተግዳሮት መሆኑን የተቋሙ የሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እሸቱ በልሁ ለኢቲቪ ተናግረዋል።
በዚህም ተደራሽነትን ከማስፋት ባልተናነሰ የተወሰዱ መሰረተ ልማቶችን በድጋሚ ማሟላት ላይ ተጠምደናል ያሉት አቶ እሸቱ፤ አንድ ትራንስፎርመር ሲሰረቅ ከ60 በላይ አባወራ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚቋረጥበት ማሳያ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የኃይል ስርቆት፣ በልማት ጠል አካላት ሆን ተብሎ የሚደረግ የኃይል መስመር ማቋረጥ፣ በተለያዩ ግንባታዎች ወቅት የሚደርስ ውድመት የተቋሙን ዕድገት እንደገታው ነው ዳይሬክተሩ ለኢቲቪ የተናገሩት።
የተጠቀሱት ድርጊቶች በተያዘው ዓመት ከ199 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲባክን ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ ተቋሙ ችግሩን ለመግታት ያለመ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር ማካሄዱን ገልጸዋል።
በውይይቱ ያለውን የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻል ብሎም የተቋሙን አወቃቀር ማጠናከር ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ተነስቷል።
ፖሊስ እና ህብረተሰቡ መሰል ድርጊቶችን ሲያስተውል መረጃ እና ማስረጃ በማጠናቀር ለፍትህ አካላት እንዲቀርቡ ማድረግ እንደሚገባው አጽንኦት ተሰጥቶበታል።
በአፎሚያ ክበበው
#EBC #EBCdotstream #EEU #infrastructuretheft