የወራሪ - ተወራሪነት ታሪክን የሻረው የኢትዮ-ጣሊያን የሁለትዮሽ ትብብር

يوم 1 أيام
የወራሪ - ተወራሪነት ታሪክን የሻረው የኢትዮ-ጣሊያን የሁለትዮሽ ትብብር

የኢትዮጵያ እና የጣሊያን ግንኙነት የጀመረው በ1880ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ መሆኑን ታሪክ ያስረዳናል። በወቅቱ ጣሊያን በበርሊን ኮንፈረንስ ስምምነት መሰረት ከአፍሪካ አህጉር በቅኝ ግዛት አማካኝነት የራሷን ድርሻ የማግኘት ዓላማ እንደነበራት ይታወቃል። 

በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ በወቅቱ ሥልጣን ለማጠናከርና እና የጦር መሣሪያ ለማግኘት የውጭ ግንኙነትን ማጎልበትን ዓላማ አድርጎ በሸዋ ራሱን ሲያዘጋጅ የነበረው የአፄ ምኒልክ አስተዳደር ይገኛል።

በዚህ መሀል ጣሊያን ራሷን በምፅዋ በኩል አጠናክራ፣ አሰብን በግል ኩባንያ አማካኝነት ገዝታ መላው ኢትዮጵያን የመያዝ እንቅስቃሴዋን አጠናክራ ብቅ ማለቷ በታሪክ ተመዝግቧል።

ጣሊያን ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲ ሽፋን ለመያዝ ካልሆነም በጦር ኃይሏ ለማሳካት በማሰብ ዝግጅቷን አጠናክራ ቀጠለች። በኋላም በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መልክ የነበረው እንቅስቃሴ በውጫሌ ውል አንቀጽ 17 ምክንያት ሲፈርስ ሀገራቱ አይቀሬ ወደ ሆነው ጦርነት አመሩ።

ኢትዮጵያውያንም በነቂስ ወጥተው በዓድዋ ጦርነት ጣሊያንን ድል አደረጉ። በዓድዋ ኢትዮጵያውያን ከነፃነታቸው የበለጠ ዋጋ የሚሰጡት ነገር እንደሌለ አረጋገጡ። የጣሊያን ኢትዮጵያን ቅኝ የመግዛት ምኞትም ህልም ሆኖ ቀረ።

ከዚያ በኋላ ነበር በሁለቱ ሀገራት መካከል መደበኛው የሁለት አቻ ሀገራት ዲፕሎሚሲ የተጀመረው። ይሁንና ከዓድዋ ድል 40 ዓመታት በኋላ ወደ ሥልጣን የመጣው የጣሊያኑ ሙሶሎኒ የሀገር ውስጥ ቀውሱን ለማርገብ ኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈጸመ።

ስሌቱ ትክክል ያልነበረው ሙሶሎኒ ግን ፋታ ካልነበረው የአምስት ዓመታት ጦርነት በኋላ ኢትዮጵያን ለቅቆ ወጣ። ጣሊያናውያን ከዓድዋ ሽንፈት በኋላ አደባባይ ወጥተው መንግሥታቸውን ተቃውመዋል።

በዚህ ተቃውሞም የወቅቱ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍራንቼስኮ ክሪስፒ ሥልጣናቸውን ሲለቅቁ፣ ጦርነቱን የመሩት ጄኔራል ኦሪየስቴ ባራቴሪ እቅዳችንን አላሳካህም በሚል ፍርድ ቤት ቀርበው ቅጣት ተወስኖባቸዋል።

ሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ከዝግጅቱ ጀምሮ ከፍተኛ የሕዝብ ተቃውሞ የገጠመው እንደነበር "Italian Anti-colonialism and the Ethiopian War" በሚል ርዕስ "ResearchGate" ላይ የታተመው የጥናት ጽሑፍ ያሳያል።

ጣሊያን ኢትዮጵያን ከመውረሯ በፊት የቤኒቶ ሙሶሎኒ መንግሥት ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ሲሠራ ነበር።

የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪክ ተቋማት የወረራውን ዝግጅት ተቃውመዋል።

በተለይም ኢንዱስትሪ ተስፋፍቶበት የነበረው የሰሜን ጣሊያን አካባቢ ማኅበረሰብ የሙሶሎኒን እርምጃ በጽኑ ሲቃወም ነበር።

ከዚህም በላይ ከፍተኛ የወረራ ተቃውሞ የተነሳው በፈረንሳይ እና በስዊዘርላንድ ከነበሩ ጣሊያናውያን፣ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ከነበሩ ፀረ-ፋሺስት አቀንቃኞች ነበር። እንደ ጣልያን ኮሚኒስት ፓርቲ ያሉ ቡድኖች የፋሺስት አገዛዙን እና ለጦርነት እያደረገው የነበረውን ዝግጅት በከፍተኛ ሁኔታ ተቃውመዋል።

እነዚህ ወገኖቸ ተቃውሟቸውን የሚገልጹ ጽሑፎችን በድብቅ በማሳተም ሕዝቡ ውስጥ ያሰራጩ ነበር። ካርሎ ሮሴሊ፣ ጋታኖ ሳልቬሚኒ እና አንቶኒዮ ግራምሺ ደግሞ ተቃውሞውን ከሚመሩት ታዋቂ ግለሰቦች መካከል ነበሩ።

ተቃዋሚዎቹ ለወረራ የሄዱ የጣሊያን ወታደሮች ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጋር እንዲወዳጁ፣ በጋራ ድምጽ ወረራውን እንዲቃወሙ እና መሣሪያዎቻቸውን ይዘው ከጦር ግንባር እንዲጠፉ ተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ ፓርማ ባሉ አካባቢዎች ደግሞ ሴቶች እና ልጆች የባበቡር ሐዲዶችን በመዝጋት ወታደሮችን ጭነው ወደ አፍሪካ የሚያጓጉዙ ባቡሮችን ሥራ ለማስተጓጎል ሞክረዋል። እንደ ጄኖዋ እና ቬኒስ ባሉ የወደብ ከተሞች የነበሩ የወደብ ሠራተኞችም የጦር መሣሪያ ጭነው ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙ መርከቦችን በማዘግየት የበኩላቸውን ተቃውሞ ገልጸዋል።

የወቅቱ የሮማ ካቶሊክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሰትን ጨምሮ አንዳንድ ምሁራን ዝምታን ቢመርጡም፤ በርካቶች ግን ጦርነቱ የጭካኔ ድርጊት እና ዓለም አቀፉን ሕግ የሚጥስ መሆኑን በመግለጽ ተቃውመውታል።

ይሁን እንጂ የውስጥ ችግሮቹን በጦርነቱ ለመሸፈን ቆርጦ የተነሳው የፋሺስት አገዛዝ እነዚህን ድምጾች ችላ በማለት ወረራውን ተግባራዊ አደረገ። ውጤቱም እንደ ተፈራው ለሀገሪቱ ቀውስን ጨምሮላት በሽንፈት ተጠናቀቀ።

የፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የታረክ ተመራማሪ ዴኒስ ቤንትሮቫቶ እና ጣሊያናዊቷ የዩኒቨርሲቲ መምህር ሲልቪያ "From a ‘Glorious Reparation' to a ‘Wretched Adventure': The Second Italo-Ethiopian War in Italian History Textbooks (1936–2020)" በሚል ርዕስ ባሳተሙት ጥናት ሁለተኛው ወረራ በጣሊያን ትምህርት ቤቶች የታሪክ መፃሕፍት ውስጥ የተሳለበትን መንገድ አትተዋል።

በዚህ ጥናታቸው እስከ 1980ዎቹ የታተሙት የታሪክ መፃሕፍት የወረራውን ትክክለኛነት ለማሳየት ጥረት ያደረጉ መሆናቸውን እና ከ1980ዎቹ በኋላ ግን ይህ አስተሳሰብ እየተቀየረ መምጣቱን አሳይተዋል።

ከነዚህ ዓመታት በኋላ ያሉት የታሪክ መማሪያ መፃሕፍት ሁለተኛ የጣሊያን ወረራ ትክክል እንዳልሆነ፣ በጦርነቱ ወቅት ወራሪው ሠራዊት የተጠቀመው የተከለከለ የመርዝ ጋዝ ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ እንደሆነ አካትተዋል።

በኋላም በኢትዮጵያ እና ጣሊያን መካከል የተጠናከረ የልማት ትብብር ግንኙነት የተጀመረው እ.አ.አ በ1976 ነው። ትኩረታቸውን በሁለትዮሽ ስምምነቶች ላይ ያደረጉ የገጠር ልማት፣ የጤና እና የትምህርት ዘርፎች ትብብሮችም መከናወን ጀመሩ። 

የሁለቱ ሀገራት ዘመናዊው ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች የሚደረጉ ጠንካራ የልማት ትብብሮችን ያማከሉ ናቸው።

በጣሊያን መንግሥት ትብብር ከተሠሩት ፕሮጀክቶች መካከል የጣና በለስ ፕሮጀክት ትልቁ የልማት ፕሮጀክት ነበር። ጣና በለስን የገነባው የጣሊያኑ ሳሊኒ ኩባንያ የውጭ ጫናዎችን ተቋቁሞ የጊቤ ግድቦችን እውን በማድረግ በኋላ ወደ ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ተዛውሯል።

ግንኙነቱ ሲጠናከር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2015 ዓ.ም ጣሊያንን ጎብኝተው ነበር። በዚያ ወቅትም የ180 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት የተፈረመ ሲሆን፣ ገንዘቡ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን እንዲሁም የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ጤና፣ ትምህርት እና ውኃ የመሳሰሉ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማሻሻል ያለመ ነበር።

ከተጠቀሰው የትብብር ስምምነት መካከልም የኢትዮጵያን ቡና ለማሻሻል የ10.5 ሚሊዮም ዩሮ፣ እንዲሁም ለሳኒቴሽን፣ ለውኃ ልማት እና ለኃይል ልማት 31.5 ሚሊዮን ዩሮ ተመድቦ ወደ ተግባር ተገብቷል።

ሰሞኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጣሊያን ይፋዊ ጉብኝት አካሂደዋል።  በጉብኝታቸውም ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ጋር የሁለቱን ሀገራት ትብብር ይበልጥ በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተመላክቷል።

ውይይቱ በኢትዮጵያ እና በጣሊያን መካከል የሁለትዮሽ ትስስርን በማጠናከር ለአዲስ ኢንቨስትመንት እና የኢኮኖሚ ትብብር ዕድሎችን መፍጠር ላይ ያተኮረ እንደነበርም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የተሳካና በርካታ ፍሬያማ ነገሮች የተገኙበት እንደነበር የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

በለሚ ታደሰ

#ebc #ebcdotstream #ethioitalyrelations


ردود الفعل
Top