በሰው ሠራሽ አስተውሎት መሪ የሆኑ ሀገራት እነማን ናቸው? ኢትዮጵያስ በዘርፉ ምን እየሰራች ነው

منذ 2 أيام
በሰው ሠራሽ አስተውሎት መሪ የሆኑ ሀገራት እነማን ናቸው? ኢትዮጵያስ በዘርፉ ምን እየሰራች ነው

የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) መስፋፋት በአንድ ክስተት የሚገለጽ ሳይሆን በፍልስፍና፣ በሂሳብ እና በኮምፒውተር ሳይንስ ውስጥ ስር እየሰደደ ያለ ቴክኖሎጂ ነው።

ይህ የሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ በእያንዳንዱ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ሥር በመስደድ ተጽዕኖ እየፈጠረ ይገኛል። 

በየዕለቱ የምንጠቀማቸው ማኅበራዊ ሚዲያዎች ይዘቶችን ከሚመራው አልጎሪዝም አንስቶ አቅጣጫን ለማወቅ እስከምንጠቀማቸው መተግበሪያዎች፣ በገንዘብ ዝውውር እና ንግድ የምንጠቀማቸው መተግበሪያዎች የሰው ሠራሽ አስተውሎት ውጤቶች እየሆኑ መጥተዋል፡፡

በርካታ ሀገራትም ይህንን በመረዳት ነው ከፍተኛ ሙዓለ ንዋያቸውን በመመደብ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን እያለሙ የሚገኙት። 

መረጃዎች እንደሚያሳዩት አሁን ላይ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም አሜሪካ ቀዳሚውን ሥፍራ የያዘች ሲሆን፣ ቻይና እየሄደችበት ባለው ፍጥነት መሪነቱን መረከቧ እንደማይቀር ይነገራል፡፡

በዚህ ጽሑፍ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በስፋት በመጠቀም በመሪነት ተርታ ያሉ አምስት ሀገራትን እንመለከታለን፡፡ 

አሜሪካ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በከፍተኛ ደረጃ በማልማት እና በማላመድ የዓለምን 61 በመቶ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ምንጭ ሆናለች፡፡ ከፍተኛ የግል ኢንቨስትመንት እና ‘ሲልከን ቫሊ የቴክኖሎጂ መንደር’ ደግሞ ዘርፉን በማልማት የላቀ አስዋጽኦ እያደረጉ ያሉ ናቸው።

አሜሪካ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በስፋት እየተጠቀመችባቸው ያሉ ዘርፎችም ፋይናንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ጤና እና ንግድ ይገኙበታል፡፡

የፋይናንስ መጭበርበርን፣ በአልጎሪዝም የታገዘ ንግድን ለማካሄድ እንዲሁም በግል የፋይናንስ ምክርን ለማግኘት እየተጠቀመችበት ሲሆን፣ 61 በመቶ የሚሆነው የአሜሪካ ፋይናንስ ዘርፍ በሰው ሠራሽ አስተውሎት እንደሚታገዝ "The 2025 Global AI Adoption Report" ላይ ተመላክቷል።

የቴክኖሎጂው ዘርፍ 85 በመቶ፣ የጤናው ዘርፍ 42 በመቶ እንዲሁም የንግድ ዘርፍ 68 በመቶ እንደሚይዝ ሪፖርቱ ላይ ተካትቷል፡፡ አሜሪካ ለዚህ ዘርፍ 37.5 ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ አድርጋለች፡፡

ቻይና በመንግሥት ደረጃ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፉ ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ የዓለም መሪ ለመሆን ስትራቴጂ ቀርጻ እየሠራች ሲሆን አሁን ላይ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች።

ሀገሪቱ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በጤና፣ በኢ-ኮሜርስ እና በስማርት ከተሞች ላይ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በስፋት እየተጠቀመችበት ነው፡፡

ኢ-ኮሜርስ እና ጤና በቅደም ተከተል 92 በመቶ ችና 76 በመቶ የያዙ ናቸው፡፡ መንግሥት ለዘርፉ 70 በሊዮን ዶላር የመደበ ሲሆን፣ ይህን በቀጣይ ዓመታት ቻይናን ቀዳሚ ለማድረግ የተያዘውን ዕቅድ እንደሚያሳካ በርካቶች እርግጠኛ ሆነው እየተናገሩ ናቸው፡፡

ዩናይትድ ኪንግደም ሦስተኛዋ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ተጠቃሚ ሀገር ነች፡፡ ሀገሪቱ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ምርምር ጠንካራ ሥራ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ሥነ ምግባርን እና ደኅንነትን ያማከለ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥነ-ምህዳርን በማስፋት ረገድ ብዙ ርቀት ሄዳለች።

የሰው ሠራሽ አስተውሎትን ለማልማት ከአንድ ቢሊዮን ፓውንድ በላይ የመደበች ሲሆን፣ የጤና እና የፋይናንስ ዘርፎች ደግሞ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን እየተጠቀሙ ያሉ የሀገሪቱ ሴክተሮች ናቸው፡፡

በአራተኛ ደረጃ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን እየተጠቀመች ያለችው ሲንጋፖር ነች፡፡ ሲንጋፖር በመንግሥት፣ በንግድ እና በማኅበራዊ አገልግሎቶቿ ላይ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በማጣመር የተሟላ ብሔራዊ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ስትራቴጂ እየተገበረች ነው።

በተለያዩ የግል እና የመንግሥት ሴክተሮች ውስጥ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ቀልጣፋ የሕዝብ አገልግሎትን በማስፈን ውጤታማ ሆናበታለች፡፡ 

ጀርመን ሌላኛዋ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ስትራቴጂ ቀርጻ በኢንዱስሪዎቿ ተግባራዊ እያደረገች ያለች ሀገር ነች፡፡ በግል እና በመንግሥት ድርጅቶች ውስጥ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ምርምር እና ልማቷን እያፋጠነችበት ትገኛለች።

አውቶሞቲቭ፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ኢንጂነሪንግ እና ጤና ሰው ሠራሽ አስተውሎትን በስፋት እየተጠቀሙ ያሉ ሴክተሮቿ ናቸው፡፡

 

ኢትዮጵያ እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት

 

ኢትዮጵያ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ስትራቴጂ ቀርጻ ለሀገራዊ ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያደርግ እየሠራችበት ትገኛለች። በአጭር ጊዜ ተወዳዳሪ የሚያደርጋትን ግልጽ ራዕይ የቀረጸች ከመሆኗም በላይ፣ ጉልህ እድገት እያሳየችበት ያለ ዘርፍ ነው። 

በ2027 ዓ.ም የቀጣናው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ማዕከል የሚያደርጋት ግልጽ ስትራቴጂም አላት፡፡ ዘርፉን አሟጥጦ መጠቀም የሚያስችል ዲጂታል ስትራቴጂም የቀረጸች ሲሆን፣ እነዚህን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ አምስት ዓመት ሆኖታል፡፡

ውጤታማነቱን የሚያፋጥኑ የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ሮቦቲክስ ልህቀት፣ የክህሎት ማሳደጊያ እና የዳታ ማዕከላት ተዘጋጅተዋል፡፡

በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በፋይናንስ እና በፀጥታ ዘርፎች ሰው ሠራሽ አስተውሎትን መጠቀም የጀመረችው ኢትዮጵያ ትልቅ እምርታም እያሳየችት ትገኛለች፡፡

በለሚ ታደሰ

#EBC #ebcdotstream #AI #EthiopianArtificialIntelligenceInstitute


ردود الفعل
Top