የስኳር ሕመም

شهر 1 منذ
የስኳር ሕመም

በዓለማችን ላይ ቅድመ ስኳር እና ስኳር ያሉባቸው ሰዎች 1 ቢሊዮን መድረሳቸውን ጥናቶች ያሳያሉ። በዚህም ምክንያት የስኳር በሽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ ሆኗል። 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ፣ የስኳር እና ሆርሞኖች ሕክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ጌታሁን ታረቀኝ ከኢቢሲ ዶት ስትሪም ጋር በነበራቸው ቆይታ የስኳር ሕመም የሚከሰተው ሰውነታችን ስኳር በትክክል መጠቀም ሳይችል ሲቀር እንደሆነ ነው የተናገሩት። 

አንድ ሰው የስኳር ሕመም አለው የሚባለው በደሙ ውስጥ የሚገኘው የስኳር መጠን ከፍ ብሎ ሲገኝ እንደሆነም ያነሳሉ። 

በደም ውስጥ የስኳር መጠን ከፍ ብሎ የሚገኘው ደግሞ ቆሽት የተባለው የሰውነት የውስጥ አካል ኢንሱሊን የተባለውን ንጥረ ነገር በበቂ መጠን ወይም ጭራሹኑ ማመንጨት ሲያቅተው ነው ብለዋል። 

የስኳር በሽታ አንዴ ከያዘ የማይድን በሽታ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ገልጸዋል። 

በ2021 በተደረገ ጥናት ከስኳር ሕመም ዓይነቶች በዓለማችን በስፋት (እስከ 80 በመቶ) ተንሰራፍቶ የሚገኘው ዓይነት 2 የሚባለው የስኳር ሕመም መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንንም ጤናማ የኑሮ ዘይቤ በመከተል መከላከል እንደሚቻል ተናግረዋል። 

በሽታው በአሁኑ ሰዓት በዓለማችን ላይ ወረርሽን በሚባል ከፍተኛ ደረጃ በመሰራጨት ላይ ያለ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

በሰውነታችን ያለውን የስኳር መጠን በማወቅ፣ የመከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀም፣ ጤናማ የኑሮ ዘይቤ በመከተል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ እንዲሁም ጤናማ ሥርዓተ ምግብን በመከተል የስኳር ሕመምን መከላከል እንደሚገባም አመላክተዋል። 

የስኳር ሕመም በዓለማችን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል ከፍተኛ የክብደት መጨመር እንደሆነ ያነሱት ዶክተር ጌታሁን፤ ለእንዲህ ዓይነቱ ውፍረት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ በምክንያትነት እንደሚጠቀስም ገልጸዋል። 

መንስዔዎቹ

  • ከፍተኛ የሆነ የካርቦሃይድሬት መጠን ያላቸውን እና በፋብሪካ የተመረቱ ምግቦችን አብዝቶ መመገብ፣
  • ቅባትነት ያላቸውን ምግቦች ማዘውተር፣
  • አልኮል አብዝቶ መጠጣት፣
  • ሲጋራ ማጨስ እና መሰል ነገሮች ለስኳር በሽታ አጋላጭ እንደሆኑ ዶክተር ጌታሁን አንስተዋል። 

ከላይ የተጠቀሱ ልማዶችን በመቀነስ የስኳር ሕመምን መከላከል እንደሚቻል ብዙ ጥናቶች እንደሚያመላክቱ ጠቅሰዋል። 

የስኳር ምርመራ በየጊዜው ማድረግ ድንገት ቢያጋጥም አስቀድሞ ችግሩን በማወቅ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል ይረዳል ሲሉም ገልጸዋል። 

በተለይ ዓይነት ሁለት ስኳር በአብዛኛው ምልክት ስለማያሳይ በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን በየጊዜው በመለካት ችግሩ ሲጋጥም የሕክምና ክትትል ማድረግ እንደሚገባም መክረዋል። 

በሜሮን ንብረት


ردود الفعل
Top