የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ በትናንትናው ዕለት (ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም) ባካሄደው ሦስተኛ ስብሰባው የተወያየባቸውን ዐበይት ጉዳዮች አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የኮሚቴው ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ሦስተኛ ስብሰባውን ሰኔ 23 ቀን 2017 አካሂዷል። ባንኩ በማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1359/2025፣ አንቀጽ 23፣ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሠረት የተቋቋመው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ከባንኩ ዋጋን ከማረጋጋት ቀዳሚ ዓላማ ጋር የተጣጣሙ የገንዘብ ፖሊሲዎችን ነድፎ ለባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምክረ-ሐሳቦችን በማቅረብ ያስጸድቃል። በዚህ ረገድ፣ ኮሚቴው የኢትዮጵያን የዋጋ ግሽበት፣ የፊስካል፣ የውጭ ኢኮኖሚ፣ የገንዘብ አቅርቦትና የፋይናነስ ዘርፍ አዝማሚያዎችን፤ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አመልካቾችን እንዲሁም በሀገር ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላይ ጉልህ አንደምታ ያላቸው ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ይገመግማል። ኮሚቴው ከእነዚህ የማክሮ ኢኮኖሚአዊ ግምገማዎችና የቅርብ ጊዜ የወደፊት እይታዎች በመነሣት በቀጣይ ተግባራዊ የሚደረጉ የገንዘብ ፖሊሲ ምክረ-ሐሳቦችን ያቀርባል።
በዚሁ መሠረት! ኮሚቴው በሦስተኛው ዙር ውይይቱ ያካተታቸው ዐበይት ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡-
የዋጋ ግሽበት፡- ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ መጥቶ በሚያዝያና በግንቦት ወር 2017 መጨረሻ 14.4 በመቶ ደርሷል። የዋጋ ግሽበትን ከፋፍለን ስናይ፣ ምግብ-ነክ የዋጋ ግሽበት ግንቦት ወር 2017 መጨረሻ 12.1 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 25.6 በመቶ ጋርሲነጻጸር ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቷል። በተመሳሳይ ወቅት 17.8 በመቶ የደረሰው ምግብ-ነክ ያልሆነ የዋጋ ግሽበት ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ ያሳየ ቢሆንም፣ ከቅርብ ወራት ወዲህ በተወሰነ መልኩ እያንሰራራ ይገኛል። ለዚህም በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ አካባቢ የተካሄደው የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ ጫና በተወሰነ መልኩ አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሚያዝያ ወር 0.1 በመቶ በግንቦት ወር 2017 ላይ ደግሞ የ0.2 በመቶ ወርሃዊ ዕድገት መመዝገቡ የዋጋ ግሽበቱ በኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው ጫና እየቀለለ መሄዱን ያመላክታል። በተመሳሳይ፤ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲንከባለል የመጣው የዋጋ ግሽበት አሁን ካለበት ደረጃ በይበልጥ መውረድና የኑሮ ውድነትም በህብረተሰቡ ላይ እያሳደረ ያለው ከባድ ጫና መቅለል እንዳለበት፣ ይህንንም ግብ ለማሳካት ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ መተግበሩን መቀጠል እንደሚገባው ኮሚቴው ተረድቶታል።
የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፡- ኮሚቴው የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ዕድገት ተጠናክሮ እንደቀጠለ ተገንዝቧል። የብሔራዊ ባንክ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አመላካቾች (Composite Index of Economic Activities) የተጠናከረ የኢኮኖሚ ዕድገት መኖሩን ያሳያሉ። ለዚህም በግብርናው ዘርፍ እየታዩ ያሉ አበረታች እንቅስቃሴዎች፣ ከውጭ ምንዛሬ አቅርቦት መሻሻል ጋር ተያይዞ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለው የምርት ዕድገት መጨመር፤ የሸቀጦች ወጪ ንግድ በተለይም የቡና እና የወርቅ ወጪ ንግድ መጠናከርና በመካሄድ ላይ የሚገኙ ትራንስፖርትና ቱሪዝምን የመሳሰሉ አገልግሎቶች መስፋፋት ለኢኮኖሚ ዕድገቱ የየራሳቸውን አዎንታዊ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
የገንዘብ ሁኔታ፡- ከቅርብ ወራት ወዲህ በገንዘብ ዝውውር አመልካቾች ረገድ ፈጣን ዕድገት ተስተውሏል። ይህም ሊሆን የቻለው፥ የብድር ፖሊሲዎች በመጠኑም ቢሆን ላላ በመደረጋቸው እንዲሁም የፊስካል እና የውጭ ዘርፍ ዕድገት በመኖሩ ነው። ለምሳሌ፣ እስከ ሰኔ ወር 2017 መጨረሻ ድረስ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚዘዋወረው የጠቅላላ ገንዘብ አቅርቦት (broad money supply) የ23.3 በመቶ ዕድገት እንደሚያሳይ፣ የባንኮች ጠቅላላ የብድር ክምችት ደግሞ 18.1 በመቶ እንደሚያድግ ተገምቷል። መሠረታዊ ገንዘብ (base money) ደግሞ ብሔራዊ ባንክከወርቅ ሽያጭ ካገኘው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት የተነሣ ይበልጥ ፈጣን ዕድገት እንደሚያሳይይጠበቃል። ይሁን እንጂ፤ ይህ ክስተት በሀገር ውስጥ ብድርም ሆነ በጠቅላላ የገንዘብ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እንዳይኖር ያደረገው፤ብሔራዊ ባንክ በአጠቃላይ የባንክ ብድር ዕድገት ላይያስቀመጠው ጣራ አሁንም ባለመነሣቱ ነው። በመሆኑም፣ የባንኮች ትርፍ ተቀማጭ ገንዘብ (excess reserve) ከፍተኛ ዓመታዊ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፤ ጠቅላላ የገንዘብ አቅርቦትና የብድር ዕድገት ግን የዋጋ ግሽበትን ታሳቢ ካላደረገው ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (nominal GDP) ዕድገት ያነስና ከተፈላጊው የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ አቋም ጋር የተጣጣመ ነው።
የወለድ ተመን ሁኔታ፡- የተለያዩ የአጭር ጊዜ የወለድ ተመኖች ከማዕከላዊ ባንክ ፖሊሲ የወለድ ተመን ከፍ የማለት አዝማሚያ ማሳየታቸውን ኮሚቴው ተገንዝቧል። ለምሳሌ፤ ከታህሳስ ወር2017 ጀምሮ የዋጋ ግሽበትን ታሳቢ ካደረገው የወለድ ተመን ጋር ሲነጻጸር የአጭር ጊዜ የወለድ ተመኖች ከዜሮ በላይ ሆነው ቀጥለዋል። ይህም አዝማሚያ ለገንዘብ ገበያ መነቃቃት አበረታች ሁኔታ መኖሩን ያመላክታል። ለምሳሌ፤ የ91-ቀን የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ የወለድ ተመን ከፍተኛ ጭማሬ በማሳየት በግንቦት ወር 2017 መጨረሻ 17.7 በመቶ ደርሷል፤ ይህም የዋጋ ግሽበትን ታሳቢ ካደረገው የወለድ ተመን ጋር ሲነጻጸር ከዜሮ በላይ ሆኖ ተመዝግቧል። በተመሳሳይመልኩ፤ ብሔራዊ ባንክ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የገንዘብ አቅርቦት መጠን ለመቆጣጠርያስችለው ዘንድ ባንኮች እርስ በእርስ የሚበዳደሩበት የ7-ቀን ቆይታ ያለውን አማካኝ የወለድ ተመን በሚፈለገው የወለድ ተመን ክልል (interest Rate Corridor) ውስጥ እንዲሆን ከባንኮች ጋርየገንዘብ ግብይት (Open Market Operations) እያደረገ ይገኛል። በመሆኑም፣ በግንቦት ወር2017 መጨረሻ ባንኮች እርስ በእርስ የሚበዳደሩበት የ7-ቀን ቆይታ ያለው አማካኝ የወለድ ተመን 17.5 በመቶ ሲሆን፣ ይህም ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው የወለድ ተመን ክልል ውስጥ መሆኑን ያሳያል። በባንኮች መካከል እየተደረገ ያለው የገንዘብ ግብይት ከፍተኛ ዕድገት በማሳየት በግንቦት ወር 2017 መጨረሻ ብር 740.2 ቢሊዮን ደርሷል።
የባንክና የፋይናንስ ዘርፍ መረጋጋት፡- የሀገሪቱ የባንክ ሥርዓት ዝቅተኛ የተበላሸ ብድር እና በቂ ካፒታል ያለው በመሆኑ ጤናማና የተረጋጋ እንደሆነ ኮሚቴው ገምግሟል። ሆኖም፤ በአንዳንድ ባንኮች ዘንድ በተወሰነ መልኩ የጥሬ ገንዘብ አክል (liquidity) እጥረት ታይቶባቸዋል። ይህም በተወሰኑ የግል ባንኮች ዘንድ በሚታየው ከፍተኛ የብድርና የተቀማጭ ሂሳብ (loan to deposit ratio) ጥምርታ የተንጸባረቀ ቢሆንም አንዳንድ ባንኮች በተወሰነ መልኩ መሻሻል አሳይተዋል። ይሁን እንጂ፣ እነዚህ የጥሬ ገንዘብ አከል ችግሮች አሁን ላይ በባንክ ለባንክ የገንዘብ ገበያ (Interbank Money Market) እና በብሔራዊ ባንክ ቋሚ የብድር አገልግሎት መፍትሔ እያገኙ ናቸው።
የፊስካል ሁኔታ፡- ኮሚቴው በበጀት ዓመቱ ጥንቃቄ የተሞላበት የፊስካል ፖሊሲ ስርዓት እንደነበርእና ይህም ከብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ተገንዝቧል። ይህም በ 2017 በጀት ዓመት የገንዘብ ሚኒስቴር ለበጀት ጉድለት ማሟያ ከብሔራዊ ባንክ ቀጥታ ብድርእንዳይወሰድ ያደረገና የማዕከላዊ ባንኩን የገንዘብ ፖሊሲ አቋም በእጅጉ የሚደግፍ ክስተት ሆኗል።
የውጭ ኢኮኖሚ ዘርፍ፡- በሐምሌ ወር 2016 ከተካሄደው ሁሉን አቀፍ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ የውጭ ኢኮኖሚ አዝማሚያ በበርካታ መመዘኛዎች ትልቅ እምርታ አሳይቷል። ይህም በወጪ ንግድና በሐዋላ እንዲሁም በካፒታል አካውንት ከፍተኛ ዕድገት የታየ ሲሆን፣ የገቢ ንግድ ግን እምብዛም ለውጥ አልታየበትም። ከዚህ ከፍተኛ ዕድገት ጋር ተያይዞ የከረንት አካውንት ጉድለት የተሻሻለ ሲሆን፣ አጠቃላይ የክፍያ ሚዛን ባለፈው ዓመት ከነበረበት ጉድለት ወጥቶ ትርፍ በማሳየት የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችትን በአራት እጥፍ ከፍ እንዲል አድርጎታል።
ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች፡- የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት የመቀነስ አዝማሚያ በማሳየት እ.ኤ.አ በ 2025 በ 2.8 በመቶ እንዲሁም በ 2026 በ 3.0 በመቶ እንደሚያድግ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) መረጃ ያመላክታል። ይህም የኢኮኖሚ ዕድገት ከተጠበቀው 3.3 በመቶ እና ቀደም ሲል በነበሩ ዓመታት ከተመዘገበው ዕድገት ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ዝቅ ያለ መሆኑ ተመላክቷል።
በተመሳሳይ መልኩ፣ የዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበት በአንዳንድ ሀገራት የማንሰራራት አዝማሚያ እንደሚያሳይ ቢገመትም በጥቅሉ ግን የመቀነስ አዝማሚያ እንደሚኖር ይጠበቃል። የዋጋ ግሽበቱ ምንም እንኳን እ.ኤ.አ በጥር ወር 2025 ከተተነበየው ያነሰ ቢሆንም እ.ኤ.አ በ 2025 መጨረሻ ወደ 4.3 በመቶ ዝቅ እንደሚል ይገመታል። ይሁን እንጂ፣ አሁን ላይ እየተስተዋሉ ያሉ የጂኦ-ፖለቲካ አዝማሚያዎች፤ በተከታታይነት እየተደረጉ ካሉ የዓለም አቀፍ የታሪፍ ማሻሻያዎች እንዲሁም እየተከስቱ ያሉ የንግድ መስተጓጉሎች በዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያደርሱ እንደሚችሉ ስጋት አለ።
የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ግምገማና ውሳኔ
ኮሚቴው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እየወሰደ ያለው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ እየታየ ላለው የዋጋ ግሽበት መርገብ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ በመረዳቱ ይኸው ጥብቅ ፖሊሲ የዋጋ ግሽበቱ በመካከለኛ ጊዜ ሊደረስበት የታሰበው የነጠላ አሃዝ ግብ እስኪሳካ ድረስ እንዲቀጥል ወስኗል።
ከዚህ እይታ በመነሣት ኮሚቴው የሚከተሉትን የገንዘብ ፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች ለቦርድ አቅርቦ አስወስኗል። በዚሁ መሠረት፡-
አንደኛ፤ የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን (National Bank Rate) አሁን ባለበት 15 በመቶ እንዲቆይ፤ብሔራዊ ባንክ ለሚሰጣቸው ቋሚ የተቀማጭ ሂሳብ አገልግሎት (standing deposit facility)! ለቋሚ የብድር አገልግሎ) (standing lending facility) የሚከፈሉ የወለድ ተመኖች ባሉበት እንዲቀጥሉ፣ እንዲሁም ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡት የግዴታ መጠባበቂያ ምጣኔ በነበረበት እንዲቆይ ተወስኗል።
ሁለተኛ፤ አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ግሽበት የመርገብ አዝማሚያ ማስቀጠል አስፈላጊ በመሆኑ አሁን ያለው 18 በመቶ ዓመታዊ የብድር ዕድገት ጣራ እስከ ተጣዩ የመስከረም ወር 2018 የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስብሰባ ጊዜ ድረስ እንዲቆይ ተወስኗል።
ሶስተኛ፣ ንግድ ባንኮች የረጅም ጊዜ የግምጃ ቤት ቦንድ (Treasury Bond) እንዲገዙ የሚያስገድደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ (MFAD/TRBO/001/2022) እንዲነሣ ተወስኗል። አሁን ላይ የመንግሥት ገቢ የማሰባሰብ አቅም በእጅጉ በመሻሻሉ፣ እንዲሁም መንግሥት የበጀት ጉድለቱን ለሟሟላት የውጭና ገበያ መር ከሆኑ የሆኑ የሃገር ውስጥ የመበደሪያ አማራጮችን እየተጠቀመ በመሆኑ በባንኮች ላይ ተጥሎ የቆየውን ይህንን አስገዳጅ መመሪያ አሁን ላይ ማንሣቱ ተገቢ መሆኑን ኮሚቴው አምኖበታል።
አራተኛ፣ የባንኮች የብድር ዕድገት ገደብ በመስከረም ወር 2018 እንደሚከለስ ታሳቢ የተደረገ ቢሆንም፣ እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ግሽበት የመርገብ እዝማሚያ ባስጠበቀ መልኩ የሚደረጉ ለውጦች ወዳልተፈለገ ልል የገንዘብ ፖሊሲ እንዲያመራ ብሔራዊ ባንክ እንደ አስፈላጊነቱ ገበያ-መር የሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎችን የሚጠቀም ይሆናል። እነዚህ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎች የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመንን፣ ከባንኮች ጋር የሚደረግ የገንዘብ ግብይትን (Open Market Operations)፤ የውጭ ምንዛሬ መሸጥ ወይም መግዛትን (foreign exchange interventions) እንዲሁም ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡትን የግዴታ መጠባበቂያ ምጣኔ መለወጥን ያካትታሉ። የዋጋ ግሽበቱ በሚፈለገው ልክ እንዲሆን ለማስቻል እነዚህ የገንዘብ ፖሊሲ መሳሪያዎች እንደ አስፈላጊነቱ በተናጠል ወይም በቅንጅት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረጋል።
በመጨረሻም ቀጣዩ የኮሚቴው ስብሰባ መስከረም ወር 2018 መጨረሻ ወይም እንደ አስፈላጊነቱ ከዚያ ቀደም ብሎ እንዲሆን ተወስኗል።
የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
ሰኔ 23 ቀን 2017