የየሕንዳዊው ሐኪም እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለ18 ዓመት የዘለቀ ደንበኝነት

منذ 12 أيام
የየሕንዳዊው ሐኪም እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለ18 ዓመት የዘለቀ ደንበኝነት

 

ላለፉት 80 ዓመታት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ከፍ አድርጎ የበረረው  የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ ከ160 በላይ አፍሪካን ከዓለም የሚያገናኙ መዳረሻዎች አሉት።

አየር መንገዱ ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም በሕንድ 6ኛ መዳረሻው ወደ ሆነችው ሃይድራባድ በረራ ሲጀምር፤ ከተሳፋሪዎች መካከል አንዱ ሕንዳዊው ዶ/ር ሲቫ ዱቢሸቲ ነበሩ። 

በሕንድ ሃይድራባድ የሜድከቨር ሆስፒታል ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ሲቫ ዱቢሸቲ ከበረራቸው በፊት በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ከኢቢሲ ዶትስትሪም ጋር አጭር ቆይታው አድርገዋል።

እ.ኤ.አ ከ2007 ጀምሮ ላለፉት 18 ዓመታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቋሚ ደንበኛ እና የሼባ ማይልስ የወርቅ ደረጃ ደንበኛ ናቸው። ይህም ከኢትዮያውያን እና ከሌሎች አፍሪካውያን ጋር የመቀራረብ እና የመተዋወቅ ዕድል እንደፈጠረላቸው ነግረውናል።

አየር መንገዱ ሰፋፊ ሥራዎችን እየሠራ፣ የቢዝነስ አገልግሎት እየሰጠ በመሆኑ የአፍሪካን ገበያ መቆጣጠር ችሏል ብለዋል።

ይህም እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመጠቀም፣ እንዲሁም ለአውሮፕላኖች ተገቢውን ጥገና በወቅቱ በማድረጉ ለደንበኞቹ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጥ አስችሎታል ብለዋል ዶ/ር ሲቫ።

ዶ/ር ሲቫ ዱቢሸቲ ከአፍሪካ ወደ ሌሎች ሀገራት ለመብረርም ሁሌም የኢትዮጵያ አየር መንገድን እንደሚጠቀሙ ነው የነገሩን።

 

አየር መንገዱ ለደንበኞቹ እና ለእንግዶች ማረፊያ የገነባው ስካይ ላይት ሆቴልን ጨምሮ ሁሌም ጥራት ያለው አገልግሎት እንደሚያገኙም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ሀገራት በትራንዚት በአዲስ አበባ ወደ ሕንድ እና ሌሎች ሀገራት ለመብረር የሚፈጀው ጊዜ ከሌሎች አንፃር ፈጣን መሆኑ ለብዙ ህንዳውያን ተማራጭ አድርጎታል ነው ያሉት።

ከአቀባበል ጀምሮ ለእንግዶች ጥራት ያላቸውን ምግቦችን በማዘጋጀት እና በማቅረብ  ጥሩ መስተንግዶ መስጠቱ፤ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን መጠቀሙ፤ በህንዳውያን ተመራጭ እንዲሆን ስለማድረጉም ጠቁመዋል።

በዚህ ምክንያትም አየር መንገዱ ህንዳውያን ብቻ ሳይሆን በርካታ የሌሎች ሀገራት ደንበኞችን ማፍራት መቻሉንም ተናግረዋል።

አየር መንገዱ በእስያ  ብዙ  የበረራ መዳረሻዎች ያሉት እንዲሁም እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን የሚጠቀም መሆኑ ተፈላጊነቱን ከፍ እንዳደረገውም ተናግረዋል።

"ባለፉት 18 ዓመታት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ስጠቀም አንድም ቀን ችግር ገጥሞኝ አያውቅም፤ እኔን ብቻ ሳይሆን ቦርሳዎቼን ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው በጥንቃቄ ተይዘው ወደ ምፈልገው ቦታ አድርሶልኛል" ብለዋል ዶ/ር ሲቫ። 

"ኢትዮጵያ እጅግ ውብ ሀገር ናት፤ ህዝቦቿም እጅግ ተግባቢ እና ጥሩዎች ናቸው፤ ለእንግዶቻቸው የሚያደርጉት አቀባበል ቆንጆ ነው፤ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ሁሉም አፍሪካውን ሕንድን ስለሚወዱ በርካታ ህንዳውያን  በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አፍሪካ እንዲመጡ እና እንዲሠሩ ምክንያት ሆኗል" ይላሉ ህንዳዊው ሐኪም።

 

በላሉ ኢታላ


ردود الفعل
Top