እስከ መጨረሻው የታመነው፤ የመጀመሪያው ወጣት የመጨረሻው ሽማግሌ፤ ለ70 ዓመታት ያልሳቀው ሐዋርያ

يوم 1 أيام
እስከ መጨረሻው የታመነው፤ የመጀመሪያው ወጣት የመጨረሻው ሽማግሌ፤ ለ70 ዓመታት ያልሳቀው ሐዋርያ

የክርስቶስ ሆኖ የተገኘ ሁሉ ይቀጠቀጣል፡፡ የሐናና ቀያፋን ያህል ጉልበት ያገኘ ማን አለ? የጭካኔያቸውን ልክ ሁሉ በአይነት በአይነቱ እያወረዱት ነው፡፡ ይህን ተመልክቶ ከክርስቶስ ጋር የሚቆም “አብሬው ነበርኩ” የሚልስ ማን ይኖራል? ግን ይህ ሁሉ አስፈሪ መከራ በሚታይበት ውጥንቅጡ በጠፋበት ሞት በሚያስናፍቅ የጭካኔ ጫፍ በነገሰበት ሰዓት ከክርስቶስ ጎን ከእናቱ ቀጥሎ አብሮት ማን ተገኘ?

ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በቆየባቸው 33 ዓመታት ብዙ ተዓምራትን እያደረገ በትምህርቱ ብዙዎችን እየመለሰ አንዳንዶችንም ለሀዋርያዊ ተልዕኮ እየመረጠ ቆይቷል። በመጨረሻ ደቀ መዛሙርቱን አስራ ሁለት አድርጎ በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወረ ሲያስተምር ብዙዎች በትምህርቱ እየተመሰጡ አብረውት ተከትለውታል።

አንዳንዶች ከኢየሱስ ክርስቶስ አንለይም ብለው በገባህበት እንግባ በሄድክበት እንሂድ ብለው የተከተሉት ናቸው። ተዓምራቱን እያዩ በየሄደበት እየተከተሉ አንዳንዶች በመንፈሳዊ አንዳንዶችን በሥጋዊ መንገድ አብረውት ተጉዘዋል።

ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ቀርበው ከነበረባቸው ደዌ የተፈወሱ፣ ችግራቸውን የቀረፉ ብዙዎች ናቸው። አንዳንዶች ረጅም ጉዞ ልመጓዝ አስበው ችግራቸው ሲፈታ ከመንገድ ተመልሰዋል። አንዳንዶች ክርስቶስን እስከመጨረሻው ሊከተሉ ምንም ቢመጣ ከእርሱ ላይለዩ ቃል ገብተዋል።

በክርስቶስ ጉዞ ውስጥ ከሀዋርያቱ ውጭ ብዙ ህዝብ እየተከተለው ባደረበት እያደሩ በዋለበት እየዋሉ ከሰማይ መና ወርዶ የተመገቡ እስራኤላውያንን ታሪክ በተግባር በዓይናቸው አይተው ሁለት ዓሣ ሲትረፈረፍ ታሪኩን ተቋድሰዋል።

እንደገበያ ህዝብ ሲከተለው የነበረው ክርስቶስ እስከመጨረሻው ህማሙን የተካፈለው አብሮትም የቆመ ማነው? በትምህርቱ ጊዜ ሁሉ አብረንህ ካልሆንን ያሉት በሰሙነ ህማማት ቁጥራቸው እየቀነሰ የመጨረሻው ሰዓት እንደሆነ እያሰበ ማን ከጉኑ ቆመ? ይህ ፈተና (የዓርብ ፈተና) ሀዋርያቱንም ሳይቀር ተፈታትኗቸዋል።

በሰሞነ ህማማት ውስጥ ይሁዳ ወደነበረው ማንነቱ አዘንብሎ ክርስቶስን በ30 ዲናር ለመሸጥ ሲዋዋል ነገሩ ያለቀ ከዚህ በኋላ ምንም የሚመጣ ነገር እንደሌል የቆጠረ ይመስላል። አብሮት ከክርስቶስ ጋር እየተዘዋወረ ትምህርቱ ሲከታተል ተዓምራቱን ሲያደርግ የተመለከተው ይሁዳ ለምን ብሎ ሲከተለው ቆየ? ያስብላል።

የሰሙነ ህማማት መከራ የክርስቶስን ደቀ መዛሙርት መፈተኑን ለተመለከተ በመከራ ውስጥ ጸንቶ መቆምን እንደሰው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። የመከራው ብዛት፣ የ“ስቀለው” እና “ግደለው” ጩኸት የአንድ አይነት ድምጾች መብዛት የማያሸብረው ማን አለ? በዛን ሰዓት ከክርስቶስ ጋር አብሬ ነብርሁ ብሎ ማን ደፍሮ ይናገራል? ማንስ የክርስቶስ ደቀመዝሙር ነኝ ይላል?

ክርስቶስ እየተገረፈና እየተሰቀለ ነው፤ ፀሐይ ጨልማለች፣ ጨረቃ ደም ለብሳለች፣ ምድር ትንቀጠቀጣለች በዚህ ሰዓት  ሐዋርያት ሸሽተዋል፡፡ አልጋህን ይዘህ ሂድ የተባለው የ38 አመቱ በሽተኛ (መጻጉዕ) በሐሰት መስክሯል፡፡ ይህቺ ቀን የክርስትና መጨረሻ የሆነ የማይታወቅ አዲስን ነገር መጀመሪያ ይመስላል። ሁሉም ነገር ያበቃና የተቆረጠ መስሏል፡፡

ሰው የመሆን ፈተና የሚባለው እንዲህ ባለው የመከራ እና ጭንቅ ወቅት ነው። በደስታ እና ሰላም ጊዜ ሁሉም ወዳጅ ነው። የመከራው ቀን ብቻቸውን የሚቆሙ ጥቂቶች ናቸው። ከእውነት ጋር እቆማለሁ የሚሉ ተፈልገው አይገኙም። እንዲህ ባለው  ጊዜ እውነተኞቹ ቢናገሩ የሚሰማቸው የለም፤ ድምጻቸውም አይሰማም።

በሰሙነ ህማማት ከሰኞ ጀምሮ እስከ ረቡዕ ቢያንስ ሐዋርያቱ ከክርስቶስ ጋር ነበሩ። ከረቡዕ በኋላ በየቀኑ ሀዋርያቱ ከክርስቶስ ጋር ለመቆም እያንዳንዷ ደቂቃ ፈተና የሆነችባቸው የዓመታት ያህል ሩቅ እና የማይታለፉ ሆነውባቸዋል። ለዚህ ነው የመጨረሻው የክርስቶስን መከራ እና ስቃይ ከእናቱ ቀጥሎ ማን አብሮት ይቆማል የሚለው ጥያቄ የገዘፈ የሚሆነው።

ዓርብ ላይ ፀሐይ ስትጨልም፣ ጨረቃ ደም ስትለብስ፣ መጋረጃ ሲቀደድ ወንጀለኞች ደስታ ሲጎናጸፉ፣ የክፉዎች ሃይል ሲጎመራ እንዴት ንጹሃን ከመስቀሉ ሥር ሆነው ማንባትን ቻሉ? እንዴት ያለ የመታመን ጥግስ ነው?

“ሁሉም የዋጠውን ጨለማ እንጂ የተሰቀለውን ብርሃን አያይም፡፡” በሚባልበት በዛች ቅጽበት ውስጥ የመጀመሪያው ወጣት የመጨረሻው ሽማግሌ ሐዋርያ ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ብቻውን ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር የተገኘው ቅዱስ ዮሐንስ የመስቀሉ ሥር ብቸኛ ታማኝ ነው።

ቅዱስ ዮሐንስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በብዙ ስሞች አክብራ ታውቀዋለች።

ፍቁረ እግዚእ፣ ነባቤ መለኮት (ታኦሎጎስ) ነባቤ መለኮት ማለት ነው በአማርኛው ደግሞ ስለመለኮት የሚናገር ማለት ነው፤ ከአባቶቹ ነብያት ከወንድሞቹ ሐዋርያት መካከል እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ምስጢረ ሥላሴን አምልቶ አስፍቶ የተናገረ የለምና።

ቅዱስ ዮሐንስ አቡቀለምሲስ ይባላል ባለ ራዕይ የራዕይ አባት ማለት ነው። ቅዱስ ዮሐንስ እስከ መስቀል ድረስ ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለውን መከራ በማየቱ ከዚያ ዕለት ጀምሮ 70 ዘመን ሙሉ ፊቱ በኅዘን የተቋጠረ በመሆኑ (ቁጽረ ገጽ) ሆኖ ኖሯል፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ዩሐንስ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ ሲሆን የመጀመሪያው ወጣት የመጨረሻው ሽማግሌ ሐዋርያ እሱ ነበር፡፡ ቅዱስ ዩሐንስ የተወለደው በገሊላ አውራጀ በቤተ ሳይዳ ነው።

ፍቅሩንና ታማኝነቱንም ጌታ በተሰቀለ ጊዜ “እሱን ያገኘ ያገኘኛል፡፡” ብሎ ሳይፈራ ከእግረ መስቀሉ በመዋል በጽኑ እምነት አስመስክሯል፡፡ ለዚህም ነው ክርስቶስ በቀራንዮ በመጨረሻዋ ሰዓት ቅዱስ ዮሐንስን ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ከእግረ መስቀሉ ሥር ባየው ጊዜ ቅድስት ድንግል ማርያምን “እነሆ ልጅሽ ይርዳሽ፣ ያጽናናሽ”፤ ብሏታል፡፡ ደቀ መዝሙሩ ቅዱስ ዮሐንስንም “እነኋት እናትህ ታጽናናህ” ብሎታል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ እንደ ጌታው ቃል ድንግል ማርያምን ወደ ቤቱ ይዟት ስለሄደ እርሷም በዮሐንስ ቤት አስራ አምስት አመት ተቀምጣለች፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ የጌታ ትንሣኤ በተነገረ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስን ቀድሞ ከመቃብረ ክርስቶስ ከጎልጎታ እንዲገኝ ያደረገው የፍቅሩ ጽናት እንደሆነ ሊቃውንት ያስተምራሉ፡፡

ከመስቀል ስር ያልተለየው ብቸኛው ሐዋርያ ቅዱስ ዮሐንስ እንደ ወንድሞቹ ሐዋርያት ደሙ ፈሶ በሰማዕትነት አይደለም የሞተው፤ በ 90 ዓመቱ ከነስጋው ተሰወረ እንጂ።

ለዚህም ነው ከሐዋርያት መካከል ሞትን ያልቀመሰ በህይወተ ሥጋ እያለ ወደ ሰማይ የተነጠቀ እንደ ሔኖክ፣ እንደ ኤልያስ በብሔረ ሕያዋን የሚኖር ሐዋርያ ለመሆን የበቃው፡፡

ጭንቁና መከራው ሳያስፈራው እንደሐዋርያቱ ሳይሸሽ እስከመጨረሻው የከርስቶስን መከራ እስከ መስቀሉ ሥር የታመነው ቅዱስ ዮሐንስ ከዓርብ ይልቅ እሁድን ያውቅ ይሆን ያስብላል። እሁድ ትንሳኤ እንደሆነ ከዚህ ሁሉ መከራ በኋል የሚመጣውን ብርሃን ያወቀ ያስመስለዋል። እንዲህ ያለው ጽናት እና ፍቅር ከወዴት ይገኛል?

 በጌቱ ላቀው 


ردود الفعل
Top