የሰሙነ ሕማማት ሳምንት አምስተኛዋ ዕለት ዓርብ ነች። ዕለቱ በተለምዶ ‘ስግደት’ ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን ምእመናን በብዛት በየአጥቢያቸው እየተገኙ የሚሰግዱበት ነው።
ካህናት እና አገልጋዮች ዕለቱን የሚገልጹ ታሪኮችን ከወንጌላት እና ድርሳናት ሲያንብቡ እና ሌሎች ዕለቱን የሚመለከቱ ተግባራትን ሲያከናውኑ ይውላሉ።
ጸሐፍት ፈሪሳውያን እና የአይሁድ ካህናት ሐሙስ እኩለ ሌሊት ለዓርብ አጥቢያ በይሁዳ ጠቋሚነት ኢየሱስ ክርስቶስን ያዙት። ለፍርድም በጲላጦስ ዘንድ አቀረቡት።
ጲላጦስ ግን ንጹህ መሆኑን ተረድቶ ሊፈታው ፈለገ፤ ነገር ግን የአይሁድ ጩኸታቸው ስለበረከተ አሳልፎ ሰጣቸው።
በሦስት ሰዓትም ይሰቀል ዘንድ ሲፈረድበት መስቀል ተሸክሞ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ወደ ተባለው ቀራንዮ ወደሚባል ቦታ ወጣ።
ይህ ስፍራ የአዳም ዐጽም የተቀበረበት እና ቦታውም የራስ ቅል እንደሚባል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ያስተምራሉ።
በዚያም የአዳም መቃብር የሆነች ዋሻ አለች፤ አይሁድም የመስቀሉን እንጨት በዚያ የአዳም መቃብር በሚገኝበት ምድር መካከል ተከሉት።
የአዳም ዐጽም ቀድሞ ከአዳም ትውልዶች ሲተላለፍ ከኖኅ ደርሷል፤ ኖኅም በጥፋት ውኃ ዘመን ወደ መርከብ አስገብቶት በኋላ መልከጼዴቅ ቀብሮታል።
ኢየሱስ ክርስቶስም አዳምን እና ልጆቹን ለማዳን ከአዳም የራስ ቅል በላይ መስቀል ተሸከሞ ተንገላታ፤ አይሁድም እየገረፉት እስከ ቀራንዮ ዳገት ጫፍ አደረሱት። ሁለቱንም እንጨት አመሳቅለው እጆቹን እና እግሮቹን ቸነከሩት፤ በዕለተ ዓርብ ሦስት ሰዓት ላይ የተፈረደው ስቅላት ቀትር ስድስት ሰዓት ላይ ተፈጸመ።
ክርስቶስ በተሰቀለበት ሰዓት ፀሐይ ጠለቀች፤ ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ምድር ጨለመች፤ ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት ብርሃናቸውን ከለከሉ፤ ምክንያቱም የፈጣሪያቸውን ዕርቃኑን ይሸፍኑ ዘንድ ነበር በማለት ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ወንጌልን አጣቅሰው ያስተምራሉ።
ዘጠኝ ሰዓት በሆነ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ "ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ፤ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ" ብሎ በታላቅ ቃል ተናገረ። ያን ጊዜ አንዱ የአይሁድ ወታደር ሮጦ ኮምጣጣ የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበርና በሰፍነግ (ስፖንጅ) አድርጎ ወደ አፉ አቀረበለት። ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ ተፈፀመ አለ። እራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን ሳልፎ ሰጠ።
በአሥራ አንድ ሰዓት ዮሴፍ እና ኒቆዲሞስ ወደ ጲላጦስ ዘንድ ቀርበው ክርስቶስን እንዲቀብሩ እንዲፈቅድላቸው ለመኑት። እሱም ሲፈቅድላቸው ሥጋውን ከመስቀል ላይ አውርደው ገንዘው በአዲስ መቃብር ቀበሩት።
በዕለተ ዓርብ ምእመናን ሁሉ በቤተ-ክርሰቲያን ተሰብስበው የክርስቶስን ሕማማት የሚያወሱ ምንባባት እየተነበቡ ይሰገዳል።
በሦስት ሰዓት፣ በስድስት ሰዓት፣ በዘጠኝ ሰዓት እና አሥራ አንድ ሰዓት ላይ የተፈፀሙ ድርጊቶችን የሚያወሱ ምንባባት ይነብባሉ። በ11 ሰዓት ክርስቶስ ከመስቀል ወርዶ ተገንዞ መቀበሩን፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በመስቀሉ ድኅነት መደረጉን በማሰብ "ንሴብሆ" ተብሎ ይዘመራል።
ሁሉ ከተፈፀመ በኋላ አባቶች የወይራ ዝንጣፊ ይዘው በምእመናኑ መካከል በመዞር ካናዘዙ በኋላ ስግደት ይሰጣሉ።
ወይራው በጥፋት ውኃ ዘመን ኖኅ ውኃው ከምድር ላይ መድረቁን ለማረጋገጥ የላካት እርግብ ይዘው የተመለሰችው የወይራ ዝንጣፊ ምሳሌ ነው።
‘ንሴብሆ’ ተብሎ የሚዘመረው በክርስቶስ ሕማም ከኃጢአት ሞት ነጻ ስላወጣን እግዚአብሔርን እናመስግነው ለማለት ነው። ‘ንሴብሆ ለእግዚአብሔር’ ከተባለ በኋላ ሳምንቱን ሙሉ ያልነበረው "እግዚአብሔር ይፍታህ" ይባላል።
ይህም "ክርስቶስ በመስቀሉ ካሣ ፈጽሞልን ከሞት ባርነት ተፈትተናል፤ ነፍሳት ከሲኦል ወጡ" ለማለት ነው። ዕለቱ መልካሙ ዓርብ (Good Friday) ይባላል።
ከክርስቶስ በፊት ማንም ሰው ሲያጠፋ በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት ይደረግ ነበር።
በተለይ በጥንት ሮማውያን እና አሶራውያን ሕግ መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ዕለት ግን ይህ ታሪክ ተቀይሮ የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የነበረው መስቀል የቤተ ክርስቲያን የድኅነት ምልክት ስላደረገው መልካሙ ዓርብ ተብሏል።
በለሚ ታደሰ