በትግራይ ክልል ተቋርጦ የነበረው የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም መርሃ ግብር ዳግም መጀመሩን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስታውቋል።
የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የሀገራት ተወካዮች በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ትግበራ ሂደት ተመልክተዋል።
የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአውሮፖ ኅብረት እና የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች በመቐለ የተሃድሶ ማዕከል በመገኘት የስራውን ሂደት ምልከታ አድርገዋል።
አሁን ላይ በትግራይ ክልል በ2 የተሃድሶ ማዕከላት የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን ገልጸዋል።
በኅዳር ወር ተጀምሮ የነበረው የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ተግባር ከሚያዚያ 2 ጀምሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል። እስካሁንም ባለው ሂደት 12 ሺህ ሰዎችን መልሶ የማቋቋም ስራ ማከናወን ተችሏል ብለዋል።
እስከ ቀጣይ 3 ወራትም 60 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ነው ያመላከቱት።
መርሐ ግብሩን በ 4 ተሃድሶ ማዕከላት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ አጋር ድርጅቶችና ሀገራትም ለመርሐ ግብሩ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠይቀዋል።
መርሐ ግብሩ ዘላቂ ሰላምን በመፍጠር ረገድ የራሱ ሚና እንደሚጫወትም ተገልጿል።