ጸሎተ ሐሙስ

منذ 2 أيام
ጸሎተ ሐሙስ

የሰሙነ ሕማማት አራተኛዋ ዕለት ሐሙስ ስትሆን ይህቺ ሐሙስ “ጸሎተ ሐሙስ” ትባላለች። ከሕማማት ሳምንት ቁርባን የሚከናወንባት ብቸኛዋ ዕለት ነች። 

ካህናት እና አገልጋዮች ዕለቱን የሚገልጡ ምንባባትን ያቀርባለሉ። ምዕመናን በቤተክርስቲያን ተገኝተው የኢየሱስ ክርስቶስን ሕማም እያሰቡ ይሰግዳሉ።

ጸሎተ ሐሙስ ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጢረ ቊርባንን ከምሥጢረ ጸሎት ጋር አዋሕዶ የገለጠበት ዕለት ነው። ክርስቶስ የመጨረሻውን እራት አዘጋጅቶ ምሥጢረ ቁርባንን የገለጠው በስምዖን ቤት ነው።

ኢየሱስም ከሐዋርያት ጋር በአንድነት መጣ፤ ስምዖንም ከቤቱ ወጥቶ ሮጦ ከእግሩ ሥር ሰገደ፤ ወደ ቤቱም ከሐዋርያት ጋር አስገባቸው።

ይሁዳ ግን ውጭ ከሻጭ እና ለዋጭ ጋር ስለሚሸጥበት ገንዘብ እየተነጋገረ ስለነበር በዚያ ሰዓት በቤቱ አልተገኘም። በመጨረሻ ግን ሳጥን ተሸክሞ መጣ፤ ጠባቂውንም እኔ የጌታ ደቀ መዝሙር ነኝ ሲለው በር ጠባቂውም የተነጠፈውን አንሥቶ አስገባው። 

በአንደኛው ሰዓት ሌሊት (ሐሙስ ለአርብ ምሽት)፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ልብሱን አኖረ፤ ማበሻ ጨርቅም አንሥቶ ወገቡን ታጠቀ። የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጥብ ዘንድ በጴጥሮስ ጀመረ፤ ጴጥሮስ ግን እኔ ባንተ ልታጠብ አይገባኝም አለ፤ እርሱም መልሶ "እውነት እውነት እልሃለሁ፤ እኔ እግርህን ካላጠብኩህ ከእኔ ጋር ዕድል ፈንታ የለህም" ሲለው ጴጥሮስ "እንዲያስ ከሆነ ራሴን እጄንም እጠበኝ" አለው። ሌሎቹንም ሐዋርያት አጠባቸው፤ አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳንም እግሩን አጠበው። 

አባቶች እንደሚሉት ክርስቶስ የይሁዳን እግር ያጠበው አሳልፎ እንደሚሰጠው ሳያውቅ ቀርቶ ሳይሆን ፍቅርን ሲያስተምረው እና ለንስሐ ጊዜ ሲሰጠው ነው። ይህም እርሱን የሚከተሉት ሁሉ ለሚወድዳቸው ሰው ብቻ ሳይሆን ለሚጠላቸው ሰውም እንኳን በጎ ማድረግ እንደሚገባ ሲያስተምር እንደሆነ ይነገራል። 

ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ‘መጽሐፈ ምሥጢር’ በተሰኘው መጽሐፋቸው ክርስቶስ ለጴጥሮስ "እኔ እግርህን ካላጠብኩህ ከእኔ ጋር ዕድል ፈንታ የለህም" ያለውን ሲተረጉሙ፣ "እኔ በአገልጋይ አምሳል እግርህ ካላጠብኩህ አንተም ከበታችህ ላሉት ራስህን ዝቅ ለማድረግ አትችልም፤ ራስህን ዝቅ ዝቅ ካላደረግህ አለቃ ልትሆን አትችልም" ለማለት ነው ብለውታል። እርሱ አምላክ፣ ፈጣሪ፣ መምህር ሳለ ዝቅ ብሎ እንዳጠባቸው እነርሱም ክህነታቸውን እና መምህርነታቸውን በትሕትና እንዲጀምሩ ሲያስተምራቸው ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከፓትርያርኩ ጀምሮ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት በየማዕረጋቸው የምእመናኑን እግር በማጠብ የኢየሱስ ክርስቶስን የትሕትና ሥራ ታስባለች።

እግራቸውን ካጠበ በኋላም “ይህ ሥጋዬ ነው ብሉ፤ ይህ ደሜ ነው ጠጡ” ብሎ ሥርዓተ ቁርባንን አሳይቷል።

ማዕዱንም እየበሉም "እውነት እውነት እላችኋለሁ! ከእናንተ መካከል አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል" አላቸው። በዚህ ጊዜም ሐዋርያት ሁሉ ደነገጡ! እርስ በርሳቸው ተያዩ፤ "እኔ እሆን? እኔ እሆን?" ተባባሉ፤ ጴጥሮስም ዮሐንስን ጠጋ ብሎ "ማነው አሳልፎ የሚሰጥህ ብለህ ጌታን ጠይቀው" አለው፤ ዮሐንስም ጠጋ ብሎ ጠየቀው ክርስቶስም "ከእኔ ጋር እጁን ከወጪቱ የሚያገባ እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል" አለ፤ ለይሁዳም ከማዕዱ ቆርሶ ሲሰጠው ማን አሳልፎ እንደሚሰጠው ገባቸው።

በለሚ ታደሰ

 


ردود الفعل
Top